በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሞጆ ከተማ አቅራቢያ በመገንባት ላይ ለሚገኘው የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግብዓቶች በራስ አቅም በሳይቱ ላይ እየተመረቱ መሆኑን በፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል የሳይት መሐንዲስ ገለፁ፡፡
መሐንዲሱ አቶ ቢኒያም ሀብታሙ እንደተናገሩት በሳይቱ ለአንከር ቦልት ስራ የሚውል ቴምፕሌት እየተዘጋጀ ነው፡፡
በፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሠራተኛ ብርቱካን አብዱ በበኩሏ በሳይቱ በራስ አቅም በሚሰራው የአንከር ቮልት ተከላ ሥራ ላይ እየተሳተፈች መሆኗን ገልፃለች፡፡
ከአሁን ቀደም በውጭ ባለሙያዎች ይከናወኑ የነበሩ ሥራዎችን በሳይቱ በራስ አቅም መስራት መቻሉ ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪና የጊዜ ብክነት እንዳዳነው ተናግራለች፡፡
እንደ ብርቱካን ገለጻ በሳይቱ በራስ አቅም የሚከናወኑ ሥራዎች ባለሙያዎች ዕውቀታቸውን እንዲያዳብሩ እድል ከመፍጠሩ በሻገር ተቋሙ ያሉትን ባለሙያዎች በመጠቀም ትልልቅ ዕቃዎችን እንዲሰራ መተማመንን የሚፈጥር ነው፡፡
የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ጋሻው በበኩላቸው በሳይቱ ለፕሮጀክቱ አስፈላጊ የሆኑ የግንባታ ግብዓቶችን በራስ አቅም ማምረት መጀመሩ ለሌሎች ፕሮጀክቶች ትልቅ ማሳያ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የተጀመሩት ሥራዎች ፕሮጀክቱ በግብዓት አቅርቦት ችግር ምክንያት እንዳይጓተት ሚናቸው የጎላ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ቴዎድሮስ በቀጣይ የባለሙያዎችን አቅም በማጎልበት ሌሎች የግንባታ ግብዓቶችን ለመስራት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
በፕሮጀክቱ ላይ በራስ አቅም እየተሰሩ ላሉት ሲቪል ሥራዎች የሚያግዙ ከ50 ሺ በላይ ብሎኬቶች በራስ አቅም በሳይቱ ማምረት መቻሉን ቀደም ሲል መዘገባችን ይታወሳል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



