በአፋር ክልል እየተፈፀመ ያለውን የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት ለማስቆም የአካባቢውን የጎሳ መሪዎችና ወጣቶች በማሳተፍ እንደሚሰሩ የገቢረሱ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ገለፁ።
የስርቆት ችግሩን ለመከላከል ከገቢረሱ ዞንና አዋሽ 7 ኪሎ ከተማ እንዲሁም ከፈንታሌ ወረዳ ከተውጣጡ አመራሮች፣ የፀጥታ ኃላፊዎች እና የጎሳ መሪዎች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱ አሊ እንደገለፁት ስርቆት የአፋር ክልል መገለጫ ባለመሆኑ በየደረጃው ያሉ አመራሮች ሊታገሉት ይገባል።
ማህበረሰቡ ነውር ነው ብሎ የተጠየፈው የስርቆት ድርጊት ለምን እንደተስፋፋ በመለየት ለችግሩ መፍትሔ ለመስጠት መስራት ይገባል ብለዋል።
እንደ ዞን አስተዳዳሪው ገለፃ የስርቆት ወንጀሉ የተደራጀና በአቀባይና ተቀባይ ሰንሰለት የተሳሰረ በመሆኑ ድርጊቱን ለማስቆም አመራሩ በቁርጠኝነት መስራት አለበት።
አመራሩና የፀጥታ አካሉ በኃላፊነት ስሜት ካልተንቀሳቀሰ በስተቀር በመሰረተ ልማቶቹ ላይ እየተፈፀመ የሚገኘውን የስርቆት ወንጀል ማስቆም አይቻልም ሲሉ ገልፀዋል።
የገቢረሱ ዞን ብልፅግና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አባሃባ ሁሴን እንደተናገሩት ስርቆቱ በየትኛውም ወገን ይፈፀም በአፋር ክልል እስከተፈፀመ ጊዜ ድረስ የክልሉን ህዝብ ስም የሚነካ በመሆኑ እስከታችኛው የአስተዳደር መዋቅር ድረስ ግንዛቤ መፍጠርና በባለቤትነት ስሜት እንዲጠበቅ ማድረግ ያስፈልጋል።
በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን ለመከላከል በየደረጃው ያለው የመንግስት መዋቅር፣ ህብረተሰቡና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እጅና ጓንት ሆነው እንዲሰሩ አሳስበዋል።
የፈንታሌ ወረዳ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ባህሩ በበኩላቸው በየደረጃው የሚገኙ የዞንና የወረዳ አመራሮች የስርቆት ወንጀሉን ለማስቀረት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ሊወጡ ይገባል ብለዋል።
ለህብረተሰቡ አገልግሎት በሚሰጡ የልማት አውታሮች ላይ የስርቆት ወንጀል የሚፈፅሙ አካላትን ለመከላከል የአጎራባች ወረዳዎች በትብብር እንዲሰሩ ነው ጥሪ ያቀረቡት።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው በአፋር ክልል በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ አካላት ላይ የሚፈፀመውን ስርቆት ለማስቀረት በዳጉ ባህላዊ የመረጃ ልውውጥ ስርዓት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ያስፈልጋል ።
በመሰረተ ልማቱ ላይ ዝርፊያ የሚፈፅሙ አካላት ብረቶቹን የፍተሻ ኬላዎች የሚያሳልፉት ቅርፃቸውን በመለውጥ በመሆኑ የፀጥታ አካላት የቁጥጥር ስርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
በተቋሙ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ክትትልና ቁጥጥር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ በበኩላቸው በመላ ሀገሪቱ በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው የስርቆት ወንጀል ወረርሽኝ አየሆነ መምጣቱን ገልፀዋል።
የዞንና የወረዳ አመራሮች ለህብረተሰቡ አገልግሎት የሚሰጡ የኃይል መሰረተ ልማቶችን የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸውም ነው ያሳሰቡት።
በተቋሙ የማዕከላዊ ሁለት ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አለማየሁ ዘበርጋ በበኩላቸው ባለፉት ዓመታት በዞኑና በከተማ አስተዳደሮቹ ስለተፈፀሙ የማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ሞሰሶዎች ስርቆት መጠንና ስርቆቱ በየትኞቹ አካባቢዎች እንደሚፈፀም ለተወያዮቹ ገለፃ አድርገዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”









