በዞኑ 507 የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች አካላት ተሰርቀዋል

በዞኑ 507 የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች አካላት ተሰርቀዋል

በዞኑ 507 የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች አካላት ተሰርቀዋል በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ባለፉት ሦስት ወራት 507 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ አካላት መሰረቃቸውን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ አንድ ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ አስታወቀ።

የተቋሙ እና የዞኑ አመራሮች ጋር በመሰረተ ልማት ላይ ስለሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎች በተወያዩበት መድረክ ላይ የሪጅኑ የቴክኒክ ባለሙያ አቶ በሱፈቃድ ባዩ እንደገለፁት በሪጅኑ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ ከ1 ሺህ 3 መቶ በላይ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶ አካላት ላይ የስርቆት ወንጀል ተፈፅሟል።

ከዚህ ውስጥ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ቦርደዴ፣ መኤሶ፣ ቡሲን አርቤ እና ኪቶን ካራ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች 507 የማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ አካላት ተሰርቀዋል።

ጉዳት የደረሰባቸውን የምሰሶ አካላት ዳግም ለመጠገን ከ2 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን ገልፀዋል።

ከ2011 እስከ 2016 ዓ.ም መጨረሻ ድረስ በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የተለያዩ ወረዳዎችና ቀበሌዎች በሚያልፉ 119 የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ምሰሶዎች ላይ 744 ብረቶች ለስርቆት እንደተዳረጉ የጠቀሱት ባለሙያው ስርቆት የተፈፀመባቸውን የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ጠግኖ ወደ ሥራ ለማስገባት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ መደረጉን አስታውሰዋል።

እንደ አቶ በሱፈቃድ ገለፃ በዞኑ እና በከተማ አስተዳደሮቹ ባለፉት ሦስት ወራት ብቻ በኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የተፈፀመው የስርቆት ወንጀል በአምስት ዓመታት ውስጥ ከተፈፀመው ዝርፊያ ጋር እጅግ ተቀራራቢ ነው።

ይህም በምዕራብ ሀረርጌ ዞን ስር በሚገኙ ወረዳዎችና ቀበሌዎች  የሚፈፀመው የስርቆት ወንጀል አሳሳቢነቱ እየጨመረ ለመምጣቱ ማሳያ ነው ብለዋል።

በአካባቢው በተደራጀ መልኩ ስርቆት የሚፈፀም መሆኑ፣ የወሰን ማስከበር ጉዳይ፣ የዞንና የወረዳ አመራሮች ቁርጠኝነት ማነስ እና የሥራ ትብብርን ከጥቅም ጋር የማያያዝ እንዲሁም ህብረተሰቡ ለፀጥታ አካላት አፋጣኝ ጥቆማ አለመስጠቱ ለስርቆቱ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጉን ነው ባለሙያው ያብራሩት።

በመሰረተ ልማቶቹ ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን ከምንጩ ለማድረቅ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ የምዕራብ ሀረርጌ ዞን እና የጭሮ ከተማ አስተዳደር በቅንጅት ሊሰሩ እንደሚገባም ነው ባለሙያው ያስገነዘቡት።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top