በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሀረርጌ ዞን ህብረተሰቡን በማንቀሳቀስ በኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎችን ማስቆም እንደሚገባ የዞኑ ጽ/ቤት ኃላፊ ገለፁ።
የጽ/ቤት ኃላፊው ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፣ ከምዕራብ ሀረርጌ ዞን እና ከተለያዩ ወረዳዎች ከተውጣጡ አመራሮች፣ የፀጥታ እና ደህንነት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከጭሮ ከተማ አስተዳደር ጋር በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ ስለሚፈፀሙ የስርቆት ወንጀሎች ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ላይ በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ስለ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አጠቃላይ ገፅታና እንደ ተቋም በኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ እየደረሱ ስላሉ ጉዳቶች አብራርተዋል።
በተቋሙ የምስራቅ አንድ ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ወርዲ መሀመድ በበኩላቸው ከ2011 እስከ 2015 ዓ.ም ድረስ ባሉት ዓመታት በዞኑና በከተማ አስተዳደሩ ስለተፈፀሙ የማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ሞሰሶዎች ስርቆት መጠንና ስርቆቱ በየትኞቹ አካባቢዎች እንደሚፈፀም ለተወያዮቹ ገለፃ አድርገዋል።
የጭሮ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መሀመድ ዑመር የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎቹ በተደራጀ መልኩ ከተሰረቁ በኋላ ፖሊሶች ቁጥጥር የሚያደርጉባቸውን የፍተሻ ጣቢያዎች አቋርጠው ስለሚያልፉ ችግሩም ሆነ መፍትሔ ያለው በእኛው እጅ ነው ብለዋል።
በአካባቢው የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎችን የሚቆርጡ፣ የሚደልሉ፣ የሚሸጡና የሚገዙ ግለሰቦችንና ለእነርሱ ሽፋን የሚሰጡ የፀጥታ አካላት የሚፈፅሙትን ወንጀል ለመከላከል ተደጋጋሚ የምክክር መድረኮች በማዘጋጀት ግንዛቤ መፍጠር እንደሚገባ ገልፀዋል።
በምዕራብ ሀረርጌ ዞን የጉምቢ ወረዳ ቦርደዴ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር ይርጋ ብሩ እንዳሉት በወረዳው በኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ የሚገኘው የስርቆት ወንጀል እጅግ በጣም አስደንጋጭ ነው።
የወረዳው ፀጥታ ዘርፍ የተሰረቁ የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች መዳረሻቸውን የመለየትና የመፈተሽ ሥራዎችን መስራቱንም ጠቁመዋል።
እንደ ኢንስፔክተር ይርጋ ገለፃ በአካባቢው ከማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶ ዝርፊያ በተጨማሪ በባቡር ሀዲድ ብረቶች ላይም መሰል ችግሮች እያጋጠሙ ይገኛሉ።
የጭሮ ከተማ አስተዳደርና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዚያድ አማን በበኩላቸው ከተማ አስተዳደሩ የመብራት መቋረጥን እንደ ፀጥታ ቾግር አድርጎ ይገነዘባል።
የስርቆት ድርጊቱ የአካባቢው መገለጫ እንዳይሆን አበክረን እንሰራለን ብለዋል።
እንደ አቶ ዚያድ ገለፃ ዝርፊያ ከሚፈፀምበት አካባቢ እስከ አዲስ አበባ ድረስ የተዘረጋ የስርቆት ሰንሰለት በመኖሩ ችግሩን ለማስቆም በጋራ መስራት ይገባል።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮች ማስተባበሪያ አንድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መንግሥቱ እንደገለፁት የኃይል መሰረተ ልማት ስርቆትን ለማስቀረት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን ለመጠቀም እየተሰራ ነው።
የምዕራብ ሀረርጌ ዞንና የጭሮ ከተማ አስተዳደርም የስርቆት ወንጀሉን ለመከላከል የቁጥጥር ሥርዓታቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።
የምዕራብ ሀረርጌ ዞን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቶፊቅ አህመድ በሰጡት የማጠቃለያ ሀሳብ ኤሌክትሪክ የህልውና ጉዳይ በመሆኑ አመራሩ በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ የሚፈፀሙ ዝርፊያዎች ላይ ትኩረት አድርጎ ሊሰራ እንደሚገባው ተናግረዋል።
የስርቆት ወንጀሉን በሚፈፅሙ ግለሰቦች ላይ ህጋዊና አስተማሪ ርምጃ በመውሰድ ድርጊቱን ማስቆም እንደሚገባም ነው አቶ ቶፊቅ ያሳሰቡት።
በውይይቱ ላይ የተሳተፉ አመራሮች ህብረተሰቡን በማንቃትና የስርቆት ወንጀሉን በመከላከል ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”









