ፕሮጀክቱን ወደ ኦፕሬሽን በማስገባት ሀገራዊ የኃይል ስብጥርን ማስፋት እንደሚገባ ተገለፀ

ፕሮጀክቱን ወደ ኦፕሬሽን በማስገባት ሀገራዊ የኃይል ስብጥርን ማስፋት እንደሚገባ ተገለፀ

የአሉቶ ላንጋኖ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን በማጠናቀቅ ለኦፕሬሽን ማብቃት እንደሚገባ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጀነሬሽን ቢዝነስ ዘርፍ አስታወቀ።

በዘርፉ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን የተመራ የሥራ ኃላፊዎች እና ባለሙያዎች ቡድን በአሉቶ ላንጋኖ የእንፋሎት ጉድጓድ (Wellhead) ፕሮጀክት እና በነባሩ የአሉቶ ጂኦተርማል የኃይል ማመንጫ ጣቢያ ላይ የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የመስክ ምልከታው የ5 የእንፋሎት ጉድጓድ ቁፋሮና የነባሩን ጣቢያ የመልሶ ጥገና ሂደት በመገምገም ቀጣይ የሥራ መመሪያዎችን ለማስተላለፍ ያለመ ነው።

ጉብኝቱ  ነባር የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችን ውጤታማነት እና ደህንነት ለማሳደግ ዘርፉ የጀመረው ተሃድሶ አካል መሆኑም ተገልጿል።

በዚሁ ወቅት ኢንጂነር ኤፍሬም ወልደኪዳን እንደተናገሩት የእንፋሎት ኃይል በሀገራዊ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ የሚኖረውን ድርሻ ለማሳደግ የአሉቶ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን ማጠናቀቅና ወደ ኦፕሬሽን ማስገባት ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ለቀጣይ የእንፋሎት ኃይል ፕሮጀክቶች መሰረት የሚሆኑ የሰው ኃይል ልማትና አቅም ግንባታ ሥራዎች ላይ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግም ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው አሳስበዋል።

በሁሉም የኦፕሬሽን የሥራ ዘርፎች ዘላቂነትን፣ ደህንነትን እና የላቀ የክዋኔ ብቃትን በማረጋገጥ ተቋማዊ ግቦችን ማሳካትና ውጤታማነትን ማሳደግ እንደሚገባም አብራርተዋል።

ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚው ከጂኦተርማል እና ከጀነሬሽን የቴክኒክ ድጋፍ የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን የፕሮጀክቱን እና የነባሩን የአሉቶ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ጣቢያን ተዟዙረው ጎብኝተዋል።

Scroll to Top