በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተጀመረውን ተቋማዊ ለውጥ በአግባቡ መምራት የሚችል የሥራ መሪ ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን የኢትዮ ፓወር አካዳሚ የአመራር ልማት ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ተናኘ መኮንን ገለጹ።
ሥራ አስኪያጇ እንደተናገሩት ተቋማዊ ለውጡን በአግባቡ ተረድቶ መምራት የሚችል አመራር ለመፍጠር የለውጥ ምንነትንና ተያያዥ ጉዳዮችን ማዕከል ያደረጉ ተከታታይ ስልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ።
ቀደም ሲል በ14 ዙሮች በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ስልጠና መሰጠቱን ያስታወሱት ወ/ሮ ተናኘ ዛሬን ጨምሮ ለአምስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ተመሳሳይ የአቅም ግንባታ ሥልጠና መጀመሩን አስታውቀዋል።
ስልጠናው የሥራ መሪዎች ስለ ተቋማዊ ለውጥ ያላቸውን ግንዛቤ በማሳደግ ለውጡ ውጤታማ እንዲሆን የተጣለባቸውን ኃላፊነት በብቃት እንዲወጡ ለማስቻል ያለመ ነው።
የተቋማዊ ለውጥ ሥራ አመራር ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ፍቅሬ በበኩላቸው ሥልጠናው በለውጥ አመራር ሂደት ላይ ወጥ የሆነ አመለካከት ያለው አመራር ለመቅረጽ ከፍተኛ እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
ለአንድ ሳምንት በሚቆየው በዚህ ስልጠና ላይ ከለውጥ ሥራ አመራር በተጨማሪ በስጋት አስተዳደር፣ በፋይናንስ፣ በአሰሪና ሠራተኛ ጉዳዮች፣ በአፈፃፀም ምዘናና ሽልማት እንዲሁም በሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የግንዛባ ማስጨበጫዎች ለሥራ መሪዎቹ እንደሚሰጥ ታውቋል።


