የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታው የሲቪል ሥራ ከ85 በመቶ በላይ ደርሷል

የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታው የሲቪል ሥራ ከ85 በመቶ በላይ ደርሷል

የገንደአርባ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራዎች አስተባባሪ አስታወቁ፡፡

አስተባባሪው አቶ ገረመው ወልደ ማርያም እንደገለፁት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው መገንባት ለቡልቡላ የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስተማማኝ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ ያስችላል።

ለኢንዱስትሪ ፓርኩ ኃይል ለማቅረብ ከአራት ዓመት በፊት ሥምምነት ቢፈረምም በወቅቱ ከውጭ ምንዛሪ እጥረት ጋር በተያያዘ ግንባታው መዘግየቱን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የሲቪል ሥራ ከ85 በመቶ በላይ መድረሱን የጠቀሱት አቶ ገረመው የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ፣ የመቆጣጠሪያ እና የኦፕሬሽን ባለሙያ መኖሪያ ቤቶች የማጠናቀቂያ ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።

እንደ አስተባባሪው ገለፃ ጣቢያውን ከአዳሚ ቱሉ – ሻሸመኔ ከሚሄደው ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ጋር ለማገናኘት ከሚያስፈልጉ 12 የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ውስጥ የ11 ምሰሶዎች የመሰረት ሥራ እና ተከላ ተጠናቋል።

ቀሪውን 1 የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶ በሚቀጥለው ሳምንት በመትከል የኮንዳክተር ሽቦ ዝርጋታ ሥራ እንደሚጀመር ነው የጠቀሱት።

በፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች አስተባባሪ አቶ ከተማው ማርቆስ እንደተናገሩት ጣቢያው እያንዳንዳቸው 50 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች ይኖሩታል።

በጣቢያው ትራንፎርመሮችን የማስቀመጥ ሥራ መከናወኑን ጠቅሰው በቀጣይም የትራንስፎርመሮቹን ክፍሎች የመገጣጠም እና የመፈተሽ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት ለማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ የሚያስፈልጉ አብዛኞቹ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ሳይት መድረሳቸውን ያነሱት አስተባባሪው በአሁኑ ወቅት ቀሪ ዕቃዎችን ከጅቡቲ ወደብ ለማጓጓዝ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

እንደ አቶ ከተማው ገለፃ የውስጥ ለውስጥ መስመር ዝርጋታውን ከመቆጣጠሪያ ክፍሉ ጋር የማገናኘት ሥራው የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ተከላ እና የትራንስፎርመር ገጠማዎች እንደተጠናቀቁ የሚጀመር ይሆናል።

በሲኖ ሃይድሮ ኩባንያ የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ይስሃቅ ኢብራሂም በበኩላቸው ፕሮጀክቱን በዕቅዱ መሠረት በጥራት ገንብቶ ለማስረከብ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የወቅቱ የአየር ሁኔታ ዝናባማ መሆን እና ከጅቡቲ የሚጓጓዙ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች በተፈለገው ፍጥነት ሳይት መድረስ አለመቻል በፕሮጀክቱ የግንባታ ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ማሳረፋቸውን አብራርተዋል።

የፕሮጀክቱን ግንባታና የዕቃ አቅርቦት የቻይናው ሲኖ ሃይድሮ ኩባንያ እንዲሁም የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩን ዝርጋታ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት መምሪያ እያከናወኑት ይገኛሉ።

Scroll to Top