የኃይል የማከፋፈያ ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የኃይል የማከፋፈያ ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ጀመረ

የአርባምንጭ ቁጥር 2 ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሥራ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት አስታወቀ።

የፕሮጀክቱ ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ አንዱዓለም መላኩ እንደገለፁት የአርባ ምንጭ 2 ማከፋፈያ ጣቢያ ከወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 ባለ 400/230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ ቀጥሎ አገልግሎት መስጠት የጀመረ የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አንዱ አካል ነው፡፡

የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያው በአርባ ምንጭ ከተማ ሊገነባ ለታሰበው የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ እና በ120 ኪሎ ሜትር ወሰን ውስጥ ለሚገኙ አካባቢዎች አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ታስቦ መገንባቱን ተናግረዋል፡፡

እንደ ተወካይ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ ማከፋፈያ ጣቢያው 476 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው ስድስት ትራንስፎርመሮች እንዲሁም አንድ ባለ 132፣ አስር ባለ 33 እና አምስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡

የኃይል መሰረተ ልማት ግንባታው የኢነርጂ ተደራሽነትን ከማስፋፋቱም በላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚታየውን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክትም ተናግረዋል፡፡

በጣቢያው የተገጠመው የጂ.አይ.ኤስ ስዊችጊር መቆጣጠሪያ የኃይል ፍሰት የቁጥጥር ሥርዓትን ከማዘመኑም ባሻገር ጥቃቅን የቴክኒክ ጉድለቶች ሲከሰቱ በፍጥነት ምላሽ ለመስጠት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ነው አቶ አንዱዓለም የገለፁት፡፡

ይህ ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት የኃይል መቆራረጥን ከመቀነሱም በላይ የኦፕሬሽን ባለሙያዎችን የሥራ ላይ ደህንነት ለማስጠበቅ አስተማማኝ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታን ሀዮሰንግ ሄቪ ኢንዱስትሪ እንዲሁም የማማከር ሥራውን ባዮክሰን ፓወር በተሰኙ የኮሪያ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች ተከናውኗል፡፡

የወላይታ ሶዶ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 2 ባለ 230 ኪሎ ቮልት እና የአርባ ምንጭ ቁጥር 2 – አርባ ምንጭ ቁጥር 2 ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ከሳምንት በፊት የፍተሻ እና ሙከራ ሥራቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸውን ይታወሳል።

Scroll to Top