በአካባቢያዊና ማህበረሰባዊ እንዲሁም በሥራ ላይ ጤናና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በተከናወነ ዳሰሳ ጥናት ላይ አውደ ጥናት ተካሄደ

በአካባቢያዊና ማህበረሰባዊ እንዲሁም በሥራ ላይ ጤናና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በተከናወነ ዳሰሳ ጥናት ላይ አውደ ጥናት ተካሄደ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የአካባቢያዊና ማህበረሰባዊ እንዲሁም በሥራ ላይ ጤናና ደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በተከናወነ የዳሰሳ ጥናት ላይ አውደ ጥናት ተካሂዷል።

በአዲስ አበባ ቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል በዛሬው ዕለት በተዘጋጀው አውደጥናት ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢትዮ ፓወር አካዳሚ ዳይሬክተር ወንድወሰን ካሳ (ዶ/ር) እንደገለፁት ተቋሙ የሀገርን ልማት የሚያረጋግጡ በርካታ የኃይል መሠረተ ልማት ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ይገኛል።

ፕሮጀክቶቹን ሲያከናውን ለማህበረሰባዊ እና አካባቢያዊ ጉዳዮች ትኩረት እንደሚሰጥ የተናገሩት ዳይሬክተሩ ጥናቱ በፕሮጀክቶች ላይ ለሚነሱ ችግሮች ቀድሞ መፍትሔ ለመስጠት በሚሰራው ሥራ ላይ የተቋሙን አቅም ለማጠናከር እንደሚያግዝ ገልፀዋል።

የዳሰሳ ጥናቱ ላለፈው አንድ ዓመት ሲከናወን የቆየ ሲሆን ሥራው ውጤታማ እንዲሆን ተቋሙ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉንም ጠቅሰዋል።

በተቋሙ የኮርፖሬት ጤናና ደህንነት ሥራ አስኪያጅ እና የጥናቱ አስተባባሪ አቶ ኮርሳ ታሬሳ በበኩላቸው የዳሰሳ ጥናቱ ከዓለም ባንክ በተገኘ ገንዘብ ኤዥያን ኮንሰልቲንግ ኢንጅነርስ በተሰኘ አማካሪ ኩባንያ አማካኝነት መካሄዱን ገልፀዋል።

ጥናቱ ተቋሙ በአካባቢያዊ፣ ማህበረሰባዊ እንዲሁም በሥራ ላይ ጤናና ደህንነት ጉዳዮች ላይ ያለበትን አቅም እና ክፍተቶችን ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ለማወቅ እንዲሁም የቀጣይ አቅጣጫዎችን ለማመላከት ታስቦ መካሄዱን ጠቅሰዋል።

እንደ አቶ ኮርሳ ገለፃ አውደ ጥናቱ አማካሪው ያከናወነውን የዳሰሳ ጥናት ግኝት በማቅረብ የተቋሙን ነባራዊ ሁኔታ የሚያሳይ መሆኑን ለማረጋገጥ እና ጥናቱን ለማጠናክር የሚያስችሉ ግብዓቶችን ከባለድርሻ አካላት ለመሰብሰብ ያለመ ነው።

የዳሰሳ ጥናቱን ለማከናወን የተቋሙን የተለያዩ ሪፖርቶች፣ ከርዕሰ ጉዳዮቹ ጋር የተያያዙ ፖሊሲዎች፣ መመሪያዎች፣ የአሰራር ሥርዓቶች፣ የተቋሙ መዋቅር፣ የሥራ ክፍሎችን አደረጃጀት፣ ቀድመው የተጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን መረጃዎች ጨምሮ በተቋሙ የተለያዩ የሥራ ቦታዎች ላይ ውይይቶችን እና ምልከታዎችን በማድረግ መረጃዎችን መሰብሰባቸውን ጥናት አድራጊው ተቋም አስታውቋል፡፡

በመድረኩ ላይ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች እና ባለመያዎች፣ የዓለም ባንክ እና ጥናቱን ያካሄደው አማካሪ ድርጅት የሥራ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች፣ የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ተወካዮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል፡፡

Scroll to Top