የቴክኒክ ችግር የገጠመውን የበለስ ትራንስፎርመር በሌላ ቀይሮ አገልግሎት ለማስጀመር በርብርብ እየተሰራ ነው

የቴክኒክ ችግር የገጠመውን የበለስ ትራንስፎርመር በሌላ ቀይሮ አገልግሎት ለማስጀመር በርብርብ እየተሰራ ነው

በበለስ 400/132/33 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ባጋጠመ የቴክኒክ ችግር ምክንያት ለረጅም ጊዜ ተቋርጦ የቆየውን የኃይል አቅርቦት ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የበለስ ኃይል ማንጫ ጣቢያ አስታወቀ፡፡

የጣቢያው ኃላፊ አቶ የወጉ ጌትዬ እንዳስታወቁት በጣቢያው ላይ 400 ኪሎ ቮልትን ወደ 132 ኪሎ ቮልት የሚቀይር 125 ሜጋ ቮልት አምፒር አቅም ባለው ትራንስፎርመር ላይ በተፈጠረ የቴክኒክ ችግር ምክንያት በመቃጠሉ ለኢንዱስትሪዎችና ለአካባቢው ነዋሪዎች የሚደርሰውን አስተማማኝ ኃይል ለዓመታት አስተጓጉሏል፡፡

ማከፋፈያ ጣቢያው በ132 ኪሎ ቮልት ለበለስ ስኳር ፋብሪካ እና በ33 ኪሎ ቮልት ደግሞ በሰሜን አቸፈር ወረዳ ሥር ለሚገኙ ከተሞች ኃይል ይሰጥ እንደነበር ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ የደረሰው ችግር በኃይል አቅርቦቱ ላይ ጫና ማሳደሩን ገልጸዋል፡፡

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለጻ የተፈጠረውን ጫና ለማቃለል ለጣቢያው አገልግሎት ከተሰራ መስመር ላይ በመቀጠል ለአካባቢው ማህበረሰብ  በቀጥታ ኃይል እንዲያገኝ ለማድረግ ሙከራ ቢጀመርም የተወሰደው ጊዚያዊ መፍትሔ በመስመሮቹ ላይ ችግር ቢደርስ  ቀጥታ ወደ ኃይል ማመንጫ ጀነሬተሩ ዘልቆ ጉዳት ስለሚያደርስ በጣቢያው ደህንነት ላይ ትልቅ ስጋት መደቀኑን አብራርተዋል፡፡

ለችግሩ ዘላቂ መፍትሄ ለመስጠት የትራንስፎርመር ግዢ ተከናውኖ ከውጭ እንዲገባ ቢደረግም በነበረው የፀጥታ ሁኔታ እና የመንገድ ችግር ለአምስት ወራት ያህል በሱልልታ ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲቆይ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የነበሩ ስጋቶች በመወገዳቸው ትራንስፎርመሩ ጣቢያው ላይ ደርሶ መገጠሙን ጠቁመው ቀሪ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ወደ ቀደመ አገልግሎት ለመመለስ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡  

Scroll to Top