የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተሽከርካሪ አስተዳደር ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን ለማረም ጥብቅ የማስተካከያ እርምጃዎች እየወሰደ መሆኑን በተቋሙ የተሽከርካሪ አስተዳደር ቢሮ አስታወቀ፡፡
የቢሮው ሥራ አስኪያጅ አቶ ዋለ ታምሬ እንደገለፁት ከተሽከርካሪ አስተዳደር ጋር በተያያዘ ተሽከርካሪዎችን ላልተፈቀደላቸው አካላት አሳልፎ መስጠትን ጨምሮ መመሪያን ያለማክበር እና የተቋሙን ተሸከርካሪ እንደ ግል ንብረት ያለመጠበቅ የአያያዝ ጉድለቶች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡
ችግሮቹን ለማረም የአያያዝ ችግር በሚፈጥሩ አሽከርካሪዎች ላይ ከሥራ ማገድን ጨምሮ ሌሎች አስተዳደራዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን ነው የገለፁት።
እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ የተሸከርካሪዎችን ደህንነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የሰርቪስ ጊዜያቸው ሳያልፍ በወቅቱ እንዲጠገኑ የማስቻል ሥራ የሁሉም ሥራ ኃላፊዎች እና አሽከርካሪዎች ኃላፊነት ሊሆን ይገባል፡፡
ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት አዳዲስ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የጠቆሙት አቶ ዋለ አዲስ ተሽከርካሪዎች ሲገዙም ሆነ ከፕሮጀክት ሲመለሱ ጥብቅ በሆነ የፍተሻ እና የርክክብ ሂደት ውስጥ እንደሚያልፉ ተናግረዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”