በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በወረቀት እየተሰራ ያለውን የጉዞ አበል የአሰራር ሂደት ወደ ዲጂታል ሥርዓት ለመቀየር እየተሰራ መሆኑን በተቋሙ የፋይናንስ ሥራ አስፈጻሚ አስታወቁ፡፡
ሥራ አስፈጻሚው አቶ አለማየሁ መንግስቱ እንዳስታወቁት ተቋሙ የጉዞ አበልን ጨምሮ የተለያዩ የአሰራር ሂደቶችን ዲጂታላይዝድ ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡
በተቋሙ እየተተገበረ ያለውን የጉዞ አበል አሰራር ወደ ዲጂታል ሥርዓት የመቀየሩ ሥራ በሦስት ምዕራፎች ተከፋፍሎ የሚተገበር ሲሆን በመጀመሪያው ምዕራፍ በኮርፖሬት ዘርፎችና በዋና ሥራ አስፈጻሚ ስር ባሉ የሥራ ክፍሎች፣ በሁለተኛው ምዕራፍ በቢዝነስ ዘርፎች እንዲሁም በሦስተኛው ምዕራፍ በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎችና በሪጂኖች ላይ ተግባራዊ እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡


የአሰራር ሂደቱን ከወረቀት ነፃ በሆነ መልኩ በሳፕ ሲስተም ለማከናወን በመጀመሪያው ምዕራፍ ተግባራዊ ከሚደረግባቸው የሥራ ክፍሎች ለተውጣጡ የሥራ መሪዎችና ሠራተኞች በአሰራር ስርዓቱ አጠቃቀም ላይ ያተኮረ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ሥልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት በተቋሙ ያለው የጉዞ አበል አሰራር ተቋሙን ለከፍተኛ የወረቀት ወጪ የሚዳርግ እና የቁጥጥር ክፍተት ያለበት መሆኑን ያስታወሱት አቶ አለማየሁ ሲስተሙ ሲተገበር ሥራዎቹን ወረቀት አልባ በማድረግ ወጭን ለመቀነስ፣ ሥራዎችን ለማቀላጠፍ እና የጉዞ አበል የቁጥጥር ስርዓቱን ለማጠናከር እንደሚያግዝ አንስተዋል፡፡
በተጨማሪም ሲስተሙ ሠራተኞች መስክ በሚሆኑበት ጊዜ የሰዓት መቆጣጠሪያውን የቅርብ ኃላፊ መሙላትና ማጽደቅ ሳይጠበቅበት በራሱ ለመሙላት፣ “ከየኮስት ሴንተሩ” የሚወጣውን የጉዞ አበል ወጭ ሪፖርት በቀላሉ ለማውጣት እና የጉዞ አበሎችን የሚያጸድቁ አካላት ባሉበት ሆነው እንዲያጸድቁ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ስልጠና እየወሰዱ ባሉ የሥራ ክፍሎች ላይ አሰራሩ ከሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግና በወረቀት የሚቀርብ የጉዞ አበል ጥያቄ ተቀባይነት እንደማይኖረው አስገንዝበዋል፡፡
በሁለተኛውና በሦስተኛው ምዕራፍ ሲስተሙ ለሚተገበርባቸው የሥራ ክፍሎች በቀጣይ ተመሳሳይ ሥልጠናዎች እንደሚሰጡ ጠቁመው አሰራሩን በአግባቡ ለመተግበር የሥራ ክፍሎች ትብብር ማድረግ እንደሚኖርባቸውም አሳስበዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”


