የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ተጠግኖ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለአገልግሎት ዝግጁ ተደረገ

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ተጠግኖ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለአገልግሎት ዝግጁ ተደረገ

የበለስ-ጃዊ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመር ከሁለት ዓመታት በኋላ ተጠግኖ ዳግም ኤሌክትሪክ ለመስጠት ዝግጁ መደረጉን የሰሜን ምዕራብ ሪጅን አስታወቀ።

በሪጅኑ የማስተላለፊያ መስመሮች ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ በላይነህ ልጅዓለም እንዳስታወቁት ከሁለት ዓመት በፊት በበለስ ባለ 400/132/ 33 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ባጋጠመ የትራንስፎርመር ችግር ምክንያት የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ ቆይቷል፡፡

የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ለረጅም ጊዜ ከአገልግሎት ውጪ ሆኖ በመቆየቱ ምክንያትም በአማራ ክልል አዊ ብሔረሰብ ዞን ጃዊ ከተማ አካባቢ ለከፍተኛ ስርቆትና ውድመት ተዳርጎ እንደነበርም አስረድተዋል።

በዚህም ሳቢያ ሰባት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች እና 18 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮንዳክተር ሽቦ መሰረቁን ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ በላይነህ ገለፃ በአሁኑ ወቅት የተሰረቁትን ሰባት የኃይል ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች እና 18 ኪሎ ሜትር የኮንዳክተር ሽቦ ዳግም በመተካት በአካባቢው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ዝግጁ ተደርጓል፡፡

በጃዊ ከተማና በዙሪያው በሚገኙ ከተሞች ላለፉት ሁለት ዓመታት ከበለስ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ በኩል ሲቀርብ የቆየውን የኤሌክትሪክ አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር የሪጅኑ ጥገና ሠራተኞች ርብርብ እያደረጉ እንደሚገኙም ነው የገለፁት።

በበለስ ባለ 400/132/33 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ እየተከናወነ የሚገኘው የትራንስፎርመር ቅየራ እና በጃዊ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የባትሪና መሰል የጥገና ሥራዎች ሲጠናቀቁ ኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሩ ዳግም አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አብራርተዋል፡፡ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሩ ጥገና መጠናቀቁን ያነሱት አቶ በላይነህ በጥገና ሥራው ላይ ርብርብ ሲያደርጉ ለነበሩ ባለሙያዎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

Scroll to Top