ማሻ ባለ 230/33 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ፕሮጀክትን ታሳቢ ያደረጉ የኢንቨስትመንት ጥያቄዎች ለከተማው መስተዳደር እየቀረቡ መሆኑን የማሻ ከተማ ከንቲባ ገለጹ፡፡
ከንቲባው አቶ ሰራዊት አየነው እንደገለፁት አካባቢው የግብርና ምርቶች በስፋት የሚመረትበት እንደመሆኑ የተለያዩ የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎችን የሚገነቡ የግል አልሚዎችን የሚስብ እምቅ ሀብት አለው፡፡
በአሁኑ ወቅትም የማከፋፈያ ጣቢያ መገንባቱን ታሳቢ ያደረጉ የማር ማቀነባበሪያ እና የአቡካዶ ዘይት መጭመቂያ ፋብሪካ ግንባታ የጀመሩ የግል አልሚዎች እንዳሉ ገልጸዋል፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ለዘመናት የቆየውን የአካባቢውን ህብረተሰብ የኃይል አቅርቦት ጥያቄ ለመመለስም ሆነ ለከተማው አጎራባች ወረዳዎች ዘርፈ ብዙ የልማት ችግሮችን ለመፍታት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ከንቲባው ተናግረዋል፡፡
ፕሮጀክቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የከተማው መስተዳደርም ሆነ የአካባቢው ማህብረሰብ እንደ ዓይኑ ብሌን በመጠበቅ አስፈላጊውን ትብብር እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ሰራዊት ይህ ትብብርም ጣቢያው አገልግሎት መስጠት ሲጀምርም የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የማሻ አገልገሎት መስጫ ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኢሞ ወኒቶ እንደገለጹት ከ70 ኪሎ ሜትር በላይ ትላልቅ ዛፎችን አቋርጦ ከመቱ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚመጣው አንድ ባለ 33 ኪሎ ቮልት መስመር በማዕከሉ ለሚገኙት 2400 ደንበኞች ያልተቆራረጠ ኃይል ለማድረስ ፈታኝ እንደነበር አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖር ከማስቻሉም ባሻገር ደንበኞችን ለማስፋት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ያላቸውን ተስፋ ተናግረዋል፡፡
የማሻ ባለ 230/33 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ከአዲስ አበባ በ636 ኪ.ሜ. ርቀት በደቡብ ምዕራብ ህዝቦች ክልል በሸካ ዞን ማሻ ከተማ እየተገነባ ይገኛል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

