
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የገዛቸውን የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪ አውቶቡሶችን ተረክቧል።
ተቋሙ ከኩባንያው ለመግዛት ስምምነት ካደረገባቸው 12 ተሸከርካሪዎች መካከል በዛሬው ዕለት አራት አውቶቡሶችንና አምስት መካከለኛ አውቶብሶችን የተረከበ ሲሆን በቀጣይም አንድ መለስተኛ አውቶቡስና ሁለት ሚኒባሶችን የሚረከብ ይሆናል፡፡
አውቶብሶቹን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጅነር አሸብር ባልቻ ከበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ባለቤትና የቦርድ ሰብሳቢ ከአቶ በላይነህ ክንዴ ተረክበዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ አውቶቡሶችን በተረከቡበት ወቅት እንደተናገሩት ተቋሙ ንፁህና ታዳሽ የኤሌክትሪክ ኃይል በማምረት ለሀገር ውስጥ ፍጆታና ለጎረቤት ሀገራት እያቀረበ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ወቅት መንግሥት በፖሊሲ ደረጃ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ተቋሙ ፖሊሲውን ለመደገፍና በዘርፉ የተሰማሩ አምራቾችን ለማበረታታት እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በዚህም የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን ተከትሎ የሚያጋጥሙ የተሸከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያዎችን እጥረት ለመቅረፍ ተቋሙ ከግል ባለሀብቶች ጋር በመቀናጀት ለመገንባት ስትራቴጂ መቀረፁንና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ጥቅም ላይ እንዲውሉ መንግሥት የተለያዩ ድጎማዎችን እያደረገ እንደሚገኝ ያነሱት ኢንጂነር አሸብር ኩባንያው ዕድሉን በመጠቀም በሀገር ውስጥ የተገጣጠሙትን ተሽከርካሪዎች ተጠቃሚ በመሆኑ መደሰታቸውን ገልፀዋል፡፡
ተቋሙ ከኩባንያው የተረከባቸው ተሸከርካሪዎች ለሠራተኛው ምቹ የሰርቪስ አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዙ ገልፀው በቀጣይም ለተቋሙ ሥራ የሚያገለግሉ አነስተኛና መለስተኛ ተሸከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ መኪና ለመቀየር እየተሰራ እንደሆነ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አስታውቀዋል፡፡
እንደ ኢንጂነር አሸብር ገለፃ የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረገ ያለውን የገንዘብ ድጋፍ ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ፋብሪካዎችን በማቋቋም በሀገሪቱ የሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ የራሱን አስተዋጽኦ እያደረገ ይገኛል፡፡
“ኩባንያውን ማገዝና መደገፍ ኢትዮጵያን መደገፍ ነው” ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተቋሙም ይህን በመገንዘብ ለባለሀብቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል፡፡
የበላይነህ ክንዴ ግሩፕ ባለቤትና የቦርድ ሰብሳቢ አቶ በላይነህ ክንዴ በበኩላቸው ኩባንያቸው በአውቶሞቲቭ መገጣጠሚያና የምግብ ማቀነባበሪያ ዘርፎች ላይ እየተሳተፈ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ኩባንያው ከዚህ በፊት ይታወቅበት ከነበረው የነዳጅ ተሸከርካሪዎች የመገጣጠም ሥራ በማስፋት ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ 500 የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በመገጣጠም ለገበያ ማቅረቡን አስታውቀዋል፡፡
የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎችን በመጠቀም በኩል የተለያዩ አሉባልታዎች እንደሚደመጡ የተናገሩት አቶ በላይነህ ድህነትን ድል ለማድረግ ቴክኖሎጂው ላይ እምነት በመጣል መጠቀም እንደሚገባም ነው ተናገሩት፡፡
ሀገሪቱ በዓመት ለነዳጅ 5 ቢሊዮን ዶላር እንደምታወጣ የተናገሩት አቶ በላይነህ የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸው ለነዳጅ የሚወጣውን ወጪ ከማስቀረት ባለፈ የአየርና የድምጽ ብክለትን ለማስወገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኩባንያው የተገጣጠሙትን የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች መጠቀም መጀመሩ ሌሎች ተቋማትና ግለሰቦች በተሸከርካሪዎቹ ላይ አመኔታ እንዲኖራቸው ዕድል እንደሚፈጥርም አመልክተዋል፡፡
የተሸከርካሪዎቹ ባትሪ ለ15 ዓመታት እንደሚያገለግል የጠቀሱት ባለሀብቱ ኩባንያው ለባትሪ የ8 ዓመት እንዲሁም ለሞተር የ5 ዓመት ዋስትና እንደሚሰጥም አስረድተዋል፡፡
ተሸከርካሪዎችን በአግባቡ ለመጠቀም ተቋሙ ለአሽከርካሪዎች አስፈላጊውን ጥቅማ ጥቅም ማሟላት እንደሚኖርበትና አሽከርካሪዎቹም በአግባቡ እንክብካቤ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ኩባንያው ተሸከርካሪዎቹን ከማቅረብ ባለፈ ለአሽከርካሪዎች አስፈላጊውን ስልጠና ለመስጠት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎችን ለማቅረብና በቀጣይ በማንኛውም መስክ ከተቋሙ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”







