የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
በተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደገለጹት ከከፍተኛ ኢንዱስትሪዎችና ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ የሀገሪቱ የኃይል ፍላጎት እያደገ መጥቷል።
ተቋሙ በሀገሪቱ ያለውን የኃይል ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን አዳዲስ የኃይል ማመንጫዎችን፣ ማከፋፈያ ጣቢያዎችንና ማስተላለፊያ መስመሮችን በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እየገነባ ይገኛል።
የማመንጨት አቅሙን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ሲሆን በአሁኑ ወቅትም ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብና ኮይሻን ጨምሮ አምስት የኃይል ማመንጫዎችን በመገንባት ላይ ይገኛል ብለዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ የተጀመሩት ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁ በአሁኑ ወቅት ያለውን የሀገሪቱን የማመንጨት አቅም ከእጥፍ በላይ በማሳደግ የሀገር ውስጥ የኃይል ፍላጎት ከማሟላት ባሻገር ለበርካታ የአፍሪካ አገራት ኃይል ለማቅረብ ምቹ መደላድልን ይፈጥራል፡፡
ነባር የማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ከማሳደግና ያረጁ የማስተላለፊያ መስመሮችን ከመቀየር ባሻገር እንደ አውሮፓያን አቆጣጠር በ2030 የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን 78 በመቶ ለማድረስ አቅዶ እየሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ ሞገስ ገለጻ ተቋሙ አሁን ላይ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን ቀለበት(ሪንግ) በማድረግ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ ጥረት እያደረገ ከመሆኑም ባሻገር ተቋሙ የኃይል ብክነትን የሚቀንሱና አሰራሩን የሚያዘምኑ ስማርት ሜትር፣ ሳፕ እና ሳውዝ ክላውድ የሚባሉ ቴክኖሎጂዎችን ሥራ ላይ አውሏል፡፡
ሆኖም ተቋሙ የሀገሪቱን የኃይል ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላትና ተደራሽነቱን ለማሳደግ በሚያደርገው ጥረት የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆት ፈተና እንደሆነበትም አብራርተዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆቱ መጠኑ ቢለያይም በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች እያጋጠመ ያለ ችግር መሆኑን ያነሱት ዳይሬክተሩ ለዚህም የሕግ ክፍተት፣ የፖለቲካ አመራሩ ቁርጠኝነት ማነስ እና የግንዛቤ እጥረት ዋነኛ ምክንያቶች መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
ለአብነትም በ2016 በጀት ዓመት ተቋሙ በስርቆት ምክንያት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም እሱን ለመጠገን ደግሞ 200 ሚሊዮን ብር በማውጣት በድምሩ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰበት ጠቁመዋል፡፡
የጎረቤት ሀገራትንና የዓለም አቀፍ ተሞክሮዎችን ልምድ በመቅሰም፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ የፖለቲካ አመራሩንና ማህበረሰቡን በማሳተፍ ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ተቋሙ እየሰራ ይገኛልም ብለዋል፡፡
የተቋሙ ሀብት የሀገር ሀብት መሆኑን በመገንዘብ የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆትን ለመከላከል ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”