
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የምስራቅ አንድ ሪጅን በሁለተኛው ምዕራፍ የሳፕ ትግበራ በሥራ ላይ በሚውለው የፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል ዙሪያ ለተጠቃሚዎች ሥልጠና እየሰጠ መሆኑን የሪጅኑ ዳይሬክተር አስታወቁ፡፡
የሪጅኑ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ወርዲ መሀመድ እንዳስታወቁት በሁለተኛው ምዕራፍ የሚተገበረው የሳፕ ፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል በሪጅኑ እየተከናወነ የሚገኘውን የጥገና ሥራ ለማዘመን ያስችላል፡፡
ሠራተኛው የሞጁሉን አሰራር ተረድቶ በአግባቡ ተግባራዊ እንዲያደርገውና የተቋሙን ዕቅድ እንዲያሳካ ሪጅኑ በተለያዩ ዙሮች ለተጠቃሚዎች ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል ብለዋል፡፡
በሪጅኑ አዘጋጅነት በሦስት ዙሮች በሚሰጠው ሥልጠና ላይ በሪጅኑ ሥር የሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊዎች፣ የማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ የጥገና ክፍል ባለሙያዎች እና ኦፕሬተሮች እንደሚሳተፉ ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ሥልጠናው ለማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊዎች በመሰጠት ላይ እንደሆነ ገልፀው በቀጣይ ለጥገና ክፍል እና ለኦፕሬተሮች ተመሳሳይ ሥልጠና በሁለት ዙሮች እንደሚሰጥ አመልክተዋል፡፡
በመረጃ አሰባሰብ፣ በጥገና አሰራር ሥርዓት፣ በመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦትና አስተዳደር፣ በመሳሪያዎች አጠቃቀም እና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ያደረገው ስልጠና በንድፈ ሀሳብና በተግባር በመታገዝ እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ወርዲ ገለፃ የፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል ሲተገበር የተቋሙን ብሎም የሪጅኑን የጊዜ፥ የገንዘብ እና የዕቃዎችን አጠቃቀምና አያያዝ በማሻሻል ሥራዎችን ያቀላጥፋል።
ከሳፕ ሥልጠና በተጨማሪ የሠራተኛውን አቅም ሊያሳድጉ የሚችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያነሱት ዳይሬክተሩ ለዚህም ከሠራተኛው ግብዓት በመሰብሰብ እና ሪጅኑ ያስፈልጋሉ ብሎ በለያቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሥልጠናዎችን በዕቅድ ላይ ተመስረቶ ለመስጠት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
የፕላንት ሜንቴናንስ ሞጁል ተጠቃሚዎች ሥልጠና በእያንዳንዱ ዙር ለአስር ቀናት የሚሰጥ ይሆናል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

