በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳይጀመሩ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው

በውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳይጀመሩ የቆዩ ፕሮጀክቶችን ለማስጀመር ጥረት እየተደረገ ነው

ከሦስት ዓመት በፊት ለግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ኃይል ለማቅረብ በዕቅድ ተይዘው የነበሩ ፕሮጀክቶችን በተያዘው በጀት ዓመት ለማስጀመር እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ ገለፀ።

በዘርፉ የአፈፃፀም ክትትልና ቁጥጥር መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አክሊሉ ታረቀኝ እንንደገለፁት ለደብረ ማርቆስ-ቡሬ፣ ገንዳ አርባ፣ ወይናታ እና ጎንደር-ዳንሻ- ሁመራ- ባዕከር የግብርና ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች ኃይል የሚያቀርቡ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ሊገኝ ባለመቻሉ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜ መጀመር አልተቻለም።

የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ ተቋሙ በዕቅድ የያዛቸውን ሥራዎች በመርሃ ግብሩ መሠረት እንዳያከናውን እንቅፋት ሆኖበት እንደቆየ ያስታወሱት አቶ አክሊሉ በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቶችን ግንባታ ማስጀመር የሚያስችል የውጭ ምንዛሪ መገኘቱን አስታውቀዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት የደብረ ማርቆስ – ቡሬ፣ ገንዳ አርባ እና ወይናታ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክቶችን ለመጀመር ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ችግሩን ለመፍታት ተቋሙ ከገንዘብ ሚኒስቴር፣ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን እና ሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶችን ሲያደርግ መቆየቱን ነው ያስረዱት።

ፕሮጀክቶቹ ከፍተኛ የሆነ የውጭ ምንዛሬ የሚጠይቁ በመሆናቸው የግንባታ ስራውን ለማስጀመር ያልተቻለ ሲሆን አሁን በተገኘው የውጭ ምንዛሪ ሦስቱ ፕሮጀክቶች በተያዘው የበጀት ዓመት እንደሚጀመሩ አቶ አክሊሉ አረጋግጠዋል፡፡

ለፕሮጀክቶች የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ችግር ሙሉ በሙሉ እስኪፈታ ተቋሙ ጥረቱን አጠናክሮ እንደሚቀጥልም ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቶቹን የግንባታ ሥራ ለመጀመር ሲታቀድ ለአራቱም ፕሮጀክቶች 4 ነጥብ 83 ቢሊዮን ብር የግንባታ ወጪ ተመድቦላቸው እንደነበር አቶ አክሊሉ አስታውሰዋል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top