
በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የሚፈጸመው ስርቆት በየዓመቱ ከሃያ በመቶ በላይ እየጨመረ መምጣቱን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ፡፡
የዘርፉ ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሀብታሙ ውቤ እንደገለጹት የሚፈጸመው ስርቆት በዚሁ ከቀጠለ ብሔራዊ የኃይል ቋቱን በማዳከም ከጥቅም ውጭ ሊያደርገው ይችላል፡፡
ከአሁን ቀደም ከፍተኛ ሥርቆት ይፈጸም የነበረው በ132 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመር ላይ የነበረ ሲሆን በአሁን ወቅት ግን ስርቆቱ ወደ 230 እና 400 ኪሎ ቮልት መስመሮችማደጉን አቶ ሀብታሙ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት በስርቆት ምክንያት ከ800 ሚሊዮን ብር በላይ እንዲሁም የደረሰውን ጉዳት ለመጠገን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ በማውጣት በድምሩ ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ጉዳት እንደደረሰበት አቶ ሀብታሙ አስታውሰዋል፡፡
በከፍተኛ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ እየተፈጸሙ ያሉ የስርቆት ድርጊቶች በዚሁ የሚቀጥሉ ከሆነ ተቋሙ ከሚደርስበት የንብረት ኪሳራ እና የኃይል ብክነቱ በላይ ብሔራዊ የኃይል ቋቱ የሚፈለገውን አገልግሎት እንዳይሰጥ ሊያደርገው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ሀብታሙ ገለጻ የብሔራዊ የኃይል ቋቱ መሰረተ ልማት ጉዳይ ከብሔራዊ ደህንነት ተለይቶ የማይታይ በመሆኑ ችግሩን በዘላቂነት ለመከላከል ሁሉም ሊረባረብ ይገባል፡፡
የሀገሪቱ የኃይል ፍጆታ በየዓመቱ ከአስራ አምስት በመቶ በላይ እያደገ መምጣቱን ያነሱት ሥራ አስፈጻሚው ይሄን ፍላጎት ለማሟላትና በአፍሪካ ተመራጭ የታዳሽ ኃይል ማዕከል ለመሆን በሚያደርገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ስጋት መደቀኑን አስታውቀዋል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ብቻ 75 የሚደርሱ ታወሮች መውደቃቸውን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ የማስተላለፊያ መስመሮቹ የሚያልፉበት መልከዓምድር አስቸጋሪ በመሆኑ በተቋሙ አቅም ብቻ ደህንነታቸውን ማረጋገጥ አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡
የሕግ አፈጻጸሙ ወጥ አለመሆን፣ የመስተዳድር አካላትና ሕብረተሰቡ በእኔነት ስሜት ችግሩን ለመቅረፍ ዝግጁ ያለመሆን እና የግንዛቤ እጥረት የሚፈጸመውን የስርቆት ድርጊት እንዳባባሰው ተናግረዋል፡፡
የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆትን ለመከላከል ተቋሙ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትን ጨምሮ ከሌሎች የጸጥታና የመስተዳድር አካላት ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማት ስርቆትን በመከላከል በኩል ሀገራዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በመላ ሀገሪቱ ከ40 ሺ በላይ የኃይል ማስተላለፊያ ተሸካሚ ምሰሶዎች፣ ከ20 ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የማስተላለፊያ መስመሮች እንዲሁም ማከፋፍያ ጣቢያን ከማከፋፍያ ጣቢያና ማከፋፍያ ጣቢያን ከኃይል ማመንጫ ለማገናኜት የሚያስችሉ 307 የማስተላለፊያ መስመሮች አሉት፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”