የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የጤና አገልግሎት ቢሮ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ6 ሺህ ለሚልቁ የተቋሙ ሠራተኞች በተመላላሸ ህክምና አገልግሎት መስጠቱን አስታወቀ፡፡
የቢሮው ተወካይ ሥራ አስኪያጅ አቶ አድማሱ ተኸልቁ እንደገለፁት የታካሚዎች አኀዝ በበጀት ዓመቱ በድግግሞች የህክምና አገልግሎት ያገኙ የተቋሙ ሠራተኞችን ቁጥር ታሳቢ ያደረገ ነው፡፡
የተቋሙ ክሊኒክ ከመደበኛ ህክምና አገልግሎት በተጨማሪ ለ143 ሠራተኞች የሥራ ላይ ድንገተኛ ህክምና አገልግሎት መሰጠቱንም ጠቁመዋል።
ክሊኒኩ ከአቅሙ በላይ የሆኑ ህክምናዎች ሲያጋጥሙት የተቋሙ ሠራተኞች የተሻለ ህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከ19 የጤና ተቋማት ጋር የውል ስምምነት በመፈፀም እየሰራ መሆኑንም ነው አቶ አድማሱ ያስታወቁት፡፡
የህክምና መገልገያ መሳሪያዎች እና የመድኃኒት አቅርቦት በሀገር ደረጃ እጥረቶች ቢኖሩም ተቋሙ መንግስታዊ ከሆነው የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ኤጀንሲ ጋር የረጅም ጊዜ ውል በመፈራረም እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡
በስምምነቱ መሠረት ከኤጀንሲው የሚያገኛቸውን የህክምና መሳሪያዎች እና መድኃኒቶች ለዋናው መ/ቤት እና በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ለሚገኙ ክሊኒኮች ማቅረቡንም ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ አድማሱ ገለፃ በዋና መስሪያ ቤት ክሊኒክ የሚገኘው አምቡላንስ በተቋቋመው የድንገተኛ ህክምና ሰጪ ቡድን በአዲስ አበባ እና በአቅራቢያው ለሚገኙ የተቋሙ ሠራተኞች ድንገተኛ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ከህክምና አገልግሎት ባሻገር በሸታን ቀድሞ ከመከላከል አንፃር የቢሮው የኤች አይ ቪ ኤድስ እና በሸታ መከላከል እና መቆጣጠር ቡድን በዋና መስሪያ ቤት፤ በኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች እና ሪጅኖች የግንዛቤ ማሰጨበጫ እና ትምህርታዊ ስልጠና መስጠቱንም ተናግረዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



