በተያዘው በጀት ዓመት ከ25 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል ለማመንጨት ታቅዷል

በተያዘው በጀት ዓመት ከ25 ሺህ ጊጋ ዋት ሰዓት በላይ ኃይል ለማመንጨት ታቅዷል

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት ከተለያዩ የኃይል ምንጮች 25 ሺህ 423 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት መታቀዱን የኃይል ማመንጫዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ ገለፀ፡፡

በዘርፉ የዕቅድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ሽፈራው እንደገለጹት በበጀት ዓመቱ ኃይል ለማመንጨት ከታቀደው ውስጥ 24 ሺህ 245 ነጥብ 11 ጊጋ ዋት ሰዓቱ ከውሃ፣ 1 ሺህ 100 ነጥብ 78 ጊጋ ዋት ሰዓቱ ከነፋስ እንዲሁም 77 ነጥብ 65 ጊጋ ዋት ሰዓቱ ከደረቅ ቆሻሻ የሚመረት ነው፡፡

የበጀት ዓመቱን ዕቅድ ለማሳካት በስድስት ማመንጫ ጣቢያዎች ጥገና የሚፈልጉ ዩኒቶችን በመጠገን ወደ ኦፕሬሽን ለመመለስ እና የጣቢያዎችን ዝግጁነት 92 በመቶ ለማድረስ ታቅዷል ብለዋል፡፡

በዚህም በአዋሽ 2ኛ፣ ጢስ አባይ 2፣ አመርቲ ነሼ፣ ፊንጫ፣ አዳማ 1ኛ እና አሸጎዳ የኃይል ማመንጫ የቆሙ ዩኒቶች ላይ አስፈላጊውን ጥገና በማከናወን ጣቢያዎች በሙሉ አቅማቸው ኃይል እንዲያመነጩ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ወ/ሮ ጥሩወርቅ ገለፃ የኢነርጅ አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ በሁሉም ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ላይ ደረጃዉን የጠበቀ የቅድመ መከላከል፤ የፍተሻ እና የጥገና ሥራዎች ይከናወናሉ፡፡

ለዚህም በበጀት ዓመቱ ለሚከናወኑ ተግባራት ዝርዝር መርሃ ግብር መቀመጡንና ሥራዎቹ በተያዘላቸው መርሃ ግብር መሰረት እንዲፈጸሙም ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል ብለዋል፡፡

ሥራ አስኪያጇ እንዳሉት ወደ ግድቦች የሚገባው የውሃ መጠን አስተማማኝ በመሆኑ፣ አዳዲስ የኃይል ማመንጫዎች ሥራ መጀመራቸው፣ የኃይል ፍላጎት እና ፈጣን የቴክኖሎጂ ዕድገት መኖራቸው በበጀት ዓመቱ ለማመንጨት የታቀደውን ኃይል ለማሳካት እንደ መልካም አጋጣሚ የሚወሰዱ ናቸው፡፡

በአንጻሩ በማመንጫ ጣቢያዎች ላይ የቴክኖሎጂ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው የቆዩ መሣሪያዎች መኖራቸው፤ በማመንጫ ጣቢያዎች አካባቢ የሚነሱ የካሳ ጥያቄዎች እንዲሁም በከፍተኛ ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት አካላት ላይ ተደጋጋሚ ስርቆቶች መፈፀማቸው ለዕቅዱ አፈፃፀም እንደስጋት መቀመጣቸውን አስረድተዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ለማመንጨት የተያዘው ዕቅድ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ4 ሺህ 449 ጊጋ ዋት ሰዓት ብልጫ ይኖረዋል።

በበጀት ዓመቱ 19 ማመንጫ ጣቢያዎች ኃይል ያመነጫሉ ተብለው ዕቅድ እንደተያዘላቸው ሥራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠ https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Scroll to Top