ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ተጨማሪ ደንበኞችን እየጠበቁ ነውየመቱ እና የበደሌ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል የሚፈልጉ ደምበኞችን እየጠበቁ መሆናቸውን የየጣቢያዎቹ ኃላፊዎች ተናገሩ።


የመቱ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ አበበ ሰይፉ እንደገለፁት የማከፋፈያ ጣቢያ የማከፋፈያ ጣቢያው አንድ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ መስመር እንዲሁም አንድ ባለ 230፣ አምስት ባለ 33 እና ሦስት ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡
ጣቢያው ከበደሌ ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል ተቀብሎ በ230 ኪሎ ቮልት ለጋምቤላ ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲሁም በ33 ኪሎ ቮልት በዙሪያው ላሉ ወረዳዎች፤ በ15 ኪሎ ቮልት ደግሞ ለመቱ ከተማና አካባቢው እንዲሁም ለመቱ ዩኒቨርሲቲ ኃይል እያቀረበ እንደሆነ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
40 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ያለው የማከፋፈያ ጣቢያው አሁን ለደንበኞች እያቀረበ ያለው ግን ግማሽ ያህሉን ብቻ በመሆኑ ጣቢያው ያለውን ተጨማሪ አዳዲስ ደንበኞችን የማስተናገድ አቅም በአግባቡ ለመጠቀም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ደንበኛ የመሳብ ሥራ ማከናወን እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
ለጋምቤላ፣ ለመቱ እና ለአጋሮ በባለ 230 ኪሎ ቮልት ኃይል እያቀረበ ያለው የበደሌ ኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሲሳይ ቀኖ በበኩላቸው በጣቢያው የአቅም ማሳደግ ሥራ ከተከናወነ በኋላ እያንዳንዳቸው 54 ሜጋ ዋት የመሸከም አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡


በጣቢያው ላይ የአቅም ማሳደግ ሥራ በመስራት 5 ባለ 15 እና 6 ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮችን እንዲኖሩት በማድረግ ተደራሽነቱን ማስፋፋት እንደተቻለም አስረድተዋል፡፡
ጣቢያው በአምስቱ ባለ 15 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ለበደሌ ከተማና ቢራ ፋብሪካ እንዲሁም በበደሌ አካባቢ ለሚገኙ የወረዳ ከተሞች ኃይል እያቀረበ ሲሆን ከ6ቱ ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪዎች ሁለት ወጪ መስመሮች ደግሞ ጨዋቃ እና ደጋ ለሚባሉ ቦታዎች ኃይል እያቀረበ መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል።
አቶ ሲሳይ እንደገለፁት ጣቢያው ካሉት 6 ዘመናዊ ብሬከሮች ውስጥ ሁለቱ ብቻ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን አራቱ ባለ 33 ኪሎ ቮልት ብሬከሮች ግን ደንበኞችን እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ቀሪ ብሬከሮችን ወደ አገልግሎት ለማስገባት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ከበደሌ ከተማ አስተዳደር ጋር ምክክር እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡





? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”