የአርባምንጭ ሁለተኛ የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ 46 በመቶ ደርሷል

የአርባምንጭ ሁለተኛ የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ 46 በመቶ ደርሷል

የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የአርባምንጭ ሁለተኛ ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ 46 በመቶ መድረሱን የፕሮጀክቱ ምዕራፍ አንድ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ገለጹ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ አንዷለም መላኩ እንደገለጹት የአርባ ምንጭ ሁለተኛ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ ከ37 ነጥብ 09 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ በጀት ተይዞለት ግንባታው የተጀመረው ሕዳር 2016 ዓ.ም ነው።

አሁን ላይ የዲዛይን ሥራው 94 በመቶ፣ የሲቪል ግንባታው 42 በመቶ የደረሰ ሲሆን 43 ሺ ሜትር ኪዩብ የመሬት ቆረጣና 39 ሺ ሜትር ኪዩብ የአፈር ሙሌት ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።

ጂ አይ ኤሴ (GIS) ስዊች ጊሮች እና ትራንስፎርመሮችን ጨምሮ የማከፋፈያ ጣቢያ አስፈላጊ ዕቃዎች ጅቡቲ ወደብ እንደሚገኙና በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ተጓጉዘው ሳይት ሲደርሱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው እንደሚጀመር ተናግረዋል፡፡

የኦፕሬተር መኖሪያ ቤቶች ኮለን ኮንክሪት የመሙላት ሥራ መከናወኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ የትራንስፎርመሮች፣ የጂአይኤስ እና የእሳት መከላከያ ዕቃዎች ማስቀመጫ ግንባታም ተጠናቋል ብለዋል።

የአርባ ምንጭ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ ቀደም ሲል የነበረውን የአርባ ምንጭ አንድን ኃይል የመስጠት አቅም በአራት እጥፍ እንደሚያሳድገው የተናገሩት አቶ አንዷለም ይህም አርባ ምንጭ ላይ ለመገንባት ለታሰበው የተቀናጀ የግብርና ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም የማከፋፈያ ጣቢያው ግንባታ ሲጠናቀቅ በ120 ኪሎ ሜትር ርቀት ውስጥ ለሚገኙ የአካባቢው ማህበረሰቦች በቀጥታ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል ጠቁመዋል።

የግንባታ ሥራውን የሚያከናውነው ሃዮሰንግ ሄቪይ ኢንደስትሪስ ኮርፖሬሽን የግንባታ ሥራ አስከኪያጅ ሚስተር ሁይኩን ሊ እንደገለጹት ኩባንያቸው ከአሁን ቀደም የሱሉሉታ – ገብረ ጉራቻ ማስተላለፊያ መስመርን ከመገንባቱ በተጨማሪ ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ በዮርዳኖስ እና በኩዌት የማከፋፈያ ጣቢያዎችን በመገንባት ልምድ እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ሥራዎችን በተያዘው የጊዜ ሰሌዳ ለማከናወን የአካባቢው የአየር ሁኔታ፣ የሲሚንቶ እጥረት፣ የማከፋፈያ ጣቢያ ዕቃዎችን ከወደብ ወደ ሳይት ለማምጣት የትራንስፖርት ችግር እንቅፋት መፍጠሩን የገለጹት ሚስተር ሊ ሆኖም ግንባታውን በታቀደለት ጊዜና ገንዘብ ለማጠናቀቅ የማካካሻ ዕቅድ ማውጣታቸውን ተናግረዋል፡፡

የአርባ ምንጭ ሁለተኛ ማከፋፈያ ጣቢያ ከወላይታ ሶዶ 230 ኪሎ ቮልት፣ ከኦሞ ኩራዝ አንድ በ230 ኪሎ ቮልት መስመርና ከአርባ ምንጭ አንድ በ132 ኪሎ ቮልት መስመር የሚገናኝ ሲሆን በ33 ኪሎ ቮልት አስር እንዲሁም በ15 ኪሎ ቮልት አምስት በድምሩ 15 ወጭ መስመሮች አሉት፡፡

የደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አርባ ምንጭ 2ኛን ጨምሮ ሽግዳንና ቲርጋ ላይ የሚገነቡ ሦስት አዳዲስ ማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ ነባሩ ወላይታ ሶዶ ሁለተኛ እና አርባምንጭ አንድ ላይ የሚከናወን የማስፋፊያ ሥራ እንዲሁም የ424 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር ግንባታ ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይፋዊ የማኅበራዊ ትስስር ገጾችን በመቀላቀል ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ያግኙ
ፌስቡክ↠https://www.facebook.com/Ethioelectric
ቴሌግራም↠https://t.me/EEPCommuication
ትዊተር ↠ https://twitter.com/EEPethiopia
ዩትዩብ ቻናል↠ https://www.youtube.com/@ethiopowermedia
ቲክቶክ አካውንት↠https://tiktok.com/@ethio_power
ድረ – ገፃ↠ http://www.eep.com.et
መስከረም 7 ቀን 2017 ዓ.ም

Scroll to Top