በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ሞጆ ከተማ አቅራቢያ በመገንባት ላይ የሚገኘው የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ ገለጹ፡፡
ሥራ አስኪያጁ አቶ ቴዎድሮስ ጋሻው እንደገለጹት ለገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ኃይል ለማቅረብ የሚገነባው ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የጀነሬተር እና የመቆጣጠሪያ ክፍሎች ግንባታ እየተከናወነ ነው።
የኦፕሬተሮች መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተጠናቆ የማጠናቀቂያ ሥራዎችን መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡
የማከፋፈያ ጣቢያውን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ለማስቀመጥ የሚያግዙ 250 የሚሆኑ የመሠረት ቁፋሮ ሥራዎች ተጠናቆ የኮንክሪት ሙሌት ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ገልፀዋል።
የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎቹ በተያዘው ዕቅድ መሠረት ሳይት ከደረሱ ፕሮጀክቱን እስከመጭው ሐምሌ 30 ድረስ ሙሉ ለሙሉ ለማጠናቀቅ ታቅዶ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
የፕሮጀክቱ ሳይት መሀንዲስ አቶ ቢኒያም ግርማ በበኩላቸው የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኃይል አቅርቦት ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች እተከናወኑ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን በተለያዩ ምዕራፎች የሚቀርብ 575 ሜጋ ቮልት አምፔር ኃይል እንደሚፈልግ የተናገሩት አቶ ቢኒያም በመገንባት ላይ የሚገኘው የማከፋፈያ ጣቢያ በመጀመሪያው ምዕራፍ 252 ሜጋ ቮልት አምፔር ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ጠቁመዋል።
የኤሌክትሮ ሜካኒካል ግንባታውን ለመጀመር የሚያስችሉ የኃይል ማስተላለፍያ እቃዎች የዲዛይን ስር ተጠናቅቆ ፍብረካ የተጀመረ መሆኑንና የማከፋፈያ ጣቢያው እቃዎች የዲዛይን ስራ እና የእቃ ፍብርካ በሂደት ላይ መሆኑን የተናገሩት አቶ ቢኒያም የማከፋፈያ ጣቢያው የሲቪል ግንባታ 37 በመቶ፣ አጠቃላይ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ደግሞ 26 በመቶ መድረሱን ገልፀዋል።
የፕሮጀክቱ ተቆጣጣሪ መሀንዲስ አቶ ለሜሣ ረጋሣ በበኩላቸው የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኃይል አቅርቦት ኘሮጀክት የሲቪል ስራ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ እና የጥራት ደረጃ እየተከናወነ ነው ብለዋል።
የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የማከፋፈያ ጣቢያ በተቋሙ የራስ ኃይል ግንባታ መምሪያ እየተገነቡ ካሉ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ መሆኑን የጠቀሱት የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ኃ/ጊዮርጊስ ለሌሎች ፕሮጀክቶች ማሳያ በሚሆን መልኩ እየተገነባና ክትትል እየተደረገበት ስለመሆኑም ተናግረዋል።
እንደዚህ ዓይነት ፕሮጀክቶችን በተቋሙ በራስ ኃይል እንዲከናወኑ የተቋሙ የሥራ አመራር እና ቦርድ ለሰጠው ዕድልና ኃላፊነትም ምስጋና አቅርበዋል።
ፕሮጀክቱ በገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለስልጣን በሚሸፈን ከ840 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የራስ ኃይል መምሪያ እየተገነባ ይገኛል።
ፕሮጀክቱ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ እንዲሁም 2 ነጥብ 6 ኪሎ ሜትር የኃይል ማስተላለፍያ መስመር ግንባታን ያካተተ ነው፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”






