የማከፋፈያ ጣቢያው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ማስቀመጫ የኮንክሪት ሙሌት እየተከናወነ ነው

የማከፋፈያ ጣቢያው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ማስቀመጫ የኮንክሪት ሙሌት እየተከናወነ ነው

የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለ 230 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ማስቀመጫ መሰረት የኮንክሪት ሙሌት እየተከናወነ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ አስታወቀ።

በዘርፉ የራስ ኃይል ግንባታ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሰሎሞን ኃ/ጊዮርጊስ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ኮንትራት ወስዶ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የማከፋፈያ ጣቢያ በሞጆ ከተማ ዙሪያ እየገነባ ይገኛል።

የጣቢያውን የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ማስቀመጫ የኮንክሪት ሙሊት ሥራ በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ለኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራው ዝግጁ ለማድረግ ከመከላክያ ግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅት ጋር ስምምነት በመፈጸም የኮንክሪት ሙሌት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።

ስምምነቱ 1 ሺ ሜትር ኪዩብ ኮንክሪት የማቅረብና የሁለት ወራት ርዝማኔ እንዳለው የጠቆሙት አቶ ሰለሞን የአንድ መቶ ሃምሳ ሜትር ኪዩብ የኮንክሪት ሙሊት ሥራው መጠናቀቁንም ተናግረዋል።

ቀሪውን የኮንክሪት ሙሊት ሥራ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ ጋሻው በበኩላቸው 250 የሚሆኑ የማከፋፈያ ጣቢያው የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች ማስቀመጫ የመሠረት ቁፋሮ ሥራ በአጭር ጊዜ በማከናወን የ132 ፓዶች የኮንክሪት ሙሌት መጠናቀቁን አብራርተዋል።

የቀሪ ፓዶችና የአራት ትራንስፎርመሮች ማስቀመጫ መሠረት የኮንክሪት ሙሌት ሥራዎች በቀጣይ ቀናት እንደሚከናወን ተናግረዋል።

የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች በምርት ሂደት ላይ እንደሚገኙ የተናገሩት ኃላፊው የኮንክሪት ሙሌት ሥራውን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ ዕቃዎቹ ሳይት እንደደረሱ የተከላ ሥራ እንደሚጀመር ጠቁመዋል።

የመከላከያ ግንባታ ግብዓቶች ማምረቻ ድርጅት የፍሬሽ ኮንክሪት ምርት ቴክኒክ ባለሙያ አቶ ሄኖክ ሻሜሮ በበኩላቸው ድርጅቱ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጋር ስምምነት በመፈጸም ሲ – 30 የተሰኘ ጥራቱን የጠበቀ የኮንክሪት ዓይነት እያቀረበ መሆኑን ተናግረዋል።

ተቋማቱ በትብብር መስራታቸው ሥራው ጥራቱን በጠበቀ መልኩ በተያዘለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ እንደሚያግዝ የጠቆሙት ባለሙያው በቀጣይም ድርጅታቸው ከተቋሙ ጋር በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በሞጆ ከተማ አቅራቢያ እየተገነባ የሚገኘው የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የማከፋፍያ ጣቢያ ፕሮጀክት 190 ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ ዕድል ፈጥሯል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top