የኢትየጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ የተከላቸው የኢነርጂ ሜትሮች የኃይል አቅርቦቱን በአንድ ማዕከል ለመቆጣጠር የሚያግዙ መሆናቸውን የኃይል ማስተላለፊያዎችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና ዘርፍ አስታወቀ፡፡
በዘርፉ የዲጂታላይዜሽንና አቅም ማሳደግ ፕሮጀክት-2 ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ሃይማኖት ተፈራ እንደገለፁት ተቋሙ የኃይል ሽያጭ ሥርዓቱን የሚከታተልባቸው የኢነርጂ ሜትሮች በሁሉም ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ተክለዋል፡፡
ተቋሙ የኢነርጂ ሜትሮችን በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ከመትከሉ በፊት ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኃይል ሽያጩን ያከናውን የነበረው በ40/60 የቀመር ስሌት ከአጠቃላይ ገቢ ላይ 60 በመቶውን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰጥበት አሰራር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በዚህም ተቋማቱ ከኃይል ሽያጭ ማግኘት የሚገባቸውን ትክክለኛ ገቢ ለማወቅ የማይችሉበት አሰራር ይከተሉ እንደነበረ ነው ሥራ አስኪያጇ የገለፁት፡፡
ወ/ሮ ሃይማኖት አክለውም አሰራሩ ለኃይል ብክነት ከመጋለጡም ባሻገር በተቋሙና በከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች መካከል አለመግባባትና አለመተማመኖችን ፈጥሮ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት 1 ሺህ 472 የኢነርጂ ሜትሮች በማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ መተከላቸውንና በዚህም ከከፍተኛ የኃይል ተጠቃሚ ደንበኞች ጋር መግባባትና መተማመን መፈጠሩን ጠቁመዋል፡፡
የኢነርጂ ሜትሮቹ ከማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ለደንበኞች የቀረበውን ኃይል በማረጋገጥ ተቋሙ በአግባቡ ገቢውን እንዲሰበስብ አስችለዋል ያሉት ሥራ አስኪያጇ የኃይል ብክነትን በመቀነስ በኩልም ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የኢነርጂ ሜትሮችን የተከላና የፍተሻ ሥራ ያከናወነው ሲመንስ ሊሚትድ የተባለ ኩባንያ መሆኑን ያወሱት ወ/ሮ ሃይማኖት ኩባንያው ባልደረሰባቸው የሰሜን እና ምዕራብ ሪጅኖች ላይ የራስ አቅምን በማጎልበት የተከላና ፍተሻ ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
የኢነርጂ ሜትሮች የሳይበር ደህንነት ቅድመ ሁኔታዎችን እንዲያሟሉ ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር ጋር በትብብር መሰራቱን ገልፀው በመሳሪያዎቹ የሳይበር ጥቃትን ለመከላከል የሚያስችል የክትትል ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

