ለአክሱም ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ ትራንስፎርመር ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው።

ለአክሱም ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ ትራንስፎርመር ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ ነው።

በአክሱም ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ተጨማሪ አንድ ትራንስፎርመር ለመትከል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ።

በዘርፉ የማከፋፈያ ጣቢያዎች የሪጅኖች ማስተባበሪያ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውዱ አስማረ እንዳስታወቁት በማከፋፈያ ጣቢያው ላይ 125 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ያለው አንድ ተጨማሪ ትራንስፎርመር ለማስቀመጥ እየተሰራ ነው።

ትራንስፎርመሩን ለመትከል በአሁኑ ወቅት የትራንስፎርመሩ የተለያዩ አክሰሰሪዎች ከተቀመጡበት የአድዋ ማከፋፈያ ጣቢያ እና ትራንስፎርመሩን ከተቀመጠበት የአክሱም ከተማ ወደ ማከፋፈያ ጣቢያው የማጓጓዝ ሥራ ዛሬ እንደሚጀመር አስታውቀዋል።

እንደ አቶ ዘውዱ ገለፃ ትራንስፎርመሩ ሲቀመጥ ከመቀሌ- አድዋ- አክሱም እና ከተከዜ- አክሱም ያለውን መስመር በቀለበት ሥርዓት በማስተሳሰር የግሪድ ሲስተሙን ለማጠናከር ያግዛል ብለዋል።

የሰሜን ሪጅን የማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ክፍለ ተስፋይ በበኩላቸው የአክሱም ማከፋፈያ ጣቢያ ከአድዋ እና ከተከዜ በሁለት ገቢ መስመሮች ኃይል እያገኘ ይገኛል ብለዋል።

የመቀሌ- አደዋ- አክሱም ባለ 132 እና የተከዜ -አክሱም ባለ 230 ኪሎ ቮልት መስመር በቀለበት ያልተያያዘ በመሆኑ በአንዱ መስመር ላይ ኃይል ከተቋረጠ ከአክሱም እና አድዋ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል የሚያገኙ አካባቢዎች ኃይል እንደሚቋረጥባቸው ተናግረዋል።

ትራንስፎርመሩ የመቀሌ -አድዋ መስመር በተለያዩ ምክንያቶች ሲቋረጥ ለአድዋ ከአክሱም እንዲሁም የተከዜ – አክሱም መስመር ሲቆረጥ ለአክሱም በአድዋ መስመር ኃይል በማቅረብ ለአካባቢዎቹ አስተማማኝ ኃይል ለማቅረብ እንደሚያስችል አስረድተዋል።

እንደ አቶ ክፍለ ገለፃ ትራንስፎርመሩ ሲተከል ከተከዜ በባለ 230 ኪሎ ቮልት የሚገባውን ኃይል ወደ 132 በመቀየር አድዋ ከመቀሌና ከአክሱም ማከፋፈያ ጣቢያዎች በሁለት መስመር ኃይል የሚያገኝበትን ዕድል ይፈጥራል።

የማከፋፈያ ጣቢያው ሦስት ትራንስፎርመሮች እንዲኖሩት ተደርጎ ዲዛይን የተደረገ እንደነበር ያስታወሱ የሥራ ኃላፊዎቹ በአሁኑ ወቅት የሚተከለው ሁለተኛው ትራንስፎርመር የፕሮጀክቱ አካል የነበረና በተለያዩ ምክንያቶች ሳይተከል የቆየ እንደሆነም አስታውቀዋል።

የአክሱም ማከፋፈያ ጣቢያ በአሁኑ ወቅት ከ18 እስከ 20 ሜጋ ዋት ኃይል በመጫን ላይ የሚገኝ ሲሆን ሦስተኛው ትራንስፎርመር ሲተከል የጣቢያውን አቅም በእጥፍ እንደሚያሳድገውም ተገልጿል።

የአክሱም ማከፋፈያ ጣቢያ ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ 50 ሜጋ ቮልት አምፔር አቅም ባለው አንድ ትራንስፎርመር አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top