በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከማዕከላዊ 3 ሪጅን ለተውጣጡ የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፍያ ጣቢያዎች ኦፐሬሽን ባለሙያዎች በእሳት አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ዙሪያ ለአንድ ሳምንት የተሰጠው ስልጠና መጠናቀቁን የሪጅኑ ጥገናና ኦፕሬሽን ኃላፊ ገለፁ።
ኃላፊው አቶ ታደሰ ገብሬ እንደገለጹት ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጋር በመተባበር ከሪጅኑ ለተውጣጡ ባለሙያዎች መሠረታዊ የእሳት እና ድንገተኛ አደጋ መከላከል ዙሪያ ስልጠና ተሰጥቷል።
ሥልጠናው በተግባርና በቴዎሪ ታገዞ መሰጠቱን የጠቆሙት ኃላፊው በሥልጠናው ላይ ከ 20 በላይ ባለሙያዎች መሳተፋቸውንም ተናግረዋል።
እንደ አቶ ታደሰ ገለጻ የሥልጠናው ዓላማ በሪጅኑ ውስጥ ባሉ የማስተላለፊያ መስመሮችንና ማከፋፍያ ጣቢያዎች ላይ የሚከሰቱ የእሳት አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ነው።
በሪጅኑ ያሉ ባለሙያዎች የእሳት አደጋን አስቀድሞ መከላከል በሚችልባቸውና ሲከሰትም መተግበር ስላለባቸው የደህንነት ሥራዎች ዙሪያ ሥልጠናው በቂ ግንዛቤ እንደፈጠረላቸውም ተናግረዋል።
በሥልጠናው ማጠቃልያ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የእሳትና የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የስልጠና ማዕከል ኃላፊ ኮማንደር አለማየሁ ጦፋ ለሰልጣኞች የምስክር ወረቀት ሰጥተዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



