የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ ባለ 400 ኪሎ ቮልት ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት ምዕራፍ አንድ ሳይት ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።
ሥራ አስኪያጁ አቶ አንዱዓለም መላኩ እንደገለፁት የብሔራዊ ኤሌክትሪክ ደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት አካል የሆነው የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ የማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራ በአሁኑ ወቅት አፈፃፀሙ 40 በመቶ ደርሷል፡፡
በዝናብ ምክንያት የፕሮጀክቱ አፈፃፀም እንዳይጓተት ለማድረግ ክረምቱ ከመግባቱ በፊት ተጨማሪ የሥራ ሰዓቶችን ተግባራዊ በማድረግ የማካካስ ሥራ መከናወኑን የተናገሩት አቶ አንዱዓለም አሁን ላይ ከ140 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የአፈር ሙሌትና ከ49 ሺህ ሜትር ኪዩብ በላይ የመሬት ቆረጣ ሥራ መከናወኑን ገልፀዋል።
የማስፋፊያ ሥራውን በታቀደለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ሊገጥሙ የሚችሉ ስጋቶችን በመከላከል፣ ከዲዛይን ጀምሮ የሥራ ተቋራጩን ዕቅድ ከአማካሪ ድርጅቱ ጋር በቅንጅት በማፅደቅ የክትትልና ቁጥጥር ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የፕሮጀክቱን አፈፃፀም በየጊዜው በመገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ እንዲሁም ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶችን በመዘርጋት የክትትልና ቁጥጥር ሥራውን ውጤታማነት ለማሳደግ እየተሰራ እንደሆነም ነው የገለፁት፡፡
የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ የማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ግንባታ በዋናነት አዲስ እየተገነቡ ለሚገኙት ለሽግዳን፣ ቲርጋ እና አርባ ምንጭ ጂ.አይ.ኤስ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኃይል ለማቅረብ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የማስፋፊያ ሥራው የኦሞ ኩራዝ ስኳር ፋብሪካዎች ከሚጠቀሙት የሸንኮራ አገዳ ተረፈ ምርት የሚመነጨውን ከ180 ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል በሽግዳንና ቲርጋ የማከፋፈያ ጣቢያዎች አማካኝነት ወደ ብሔራዊ የኃይል ቋት ለማስገባት ያለመ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡
ይህም የኢነርጂ ስብጥሩን ከፍ ከማድረጉም በተጨማሪ በሀገሪቱ ያለውን የኃይል አቅርቦት አቅም የሚያሳድግ ነው ብለዋል፡፡
በደቡብ ኢትዮጵያ ኃይል እያቀረቡ የሚገኙት አብዛኞቹ የማስተከላለፊያ መስመሮች ባለ 132 ኪሎ ቮልት ከመሆናቸውም ባሻገር ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ በመቆየታቸው ሳቢያ አሁን ያለውን የኃይል ፍላጎት ጥያቄ ለማስተናገድ እንደማይችሉ አቶ አንዱዓለም አስታውሰዋል፡፡
የማስፋፊያ ሥራው ነባሩን የወላይታ ሶዶ ማከፋፈያ ጣቢያ አቅም በ500 ሜጋ ቮልት አምፒር የሚያሳድግና ለኃይል ፍላጎት ጥያቄዎች ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የሃዮሰንግ ሄቪይ ኢንደስትሪስ ኮርፖሬሽን የሲቪል ሥራዎች ሥራ አስኪያጅ አቶ አቤኔዘር አለማየሁ በበኩላቸው የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ የማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራ እያንዳንዳቸው 250 ሜጋ ቮልት አምፒር የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮች ተከላ ሥራን የሚያካትት ነው ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የማስፋፊያ ግንባታው የሲቪል ሥራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ትራንስፎርመሮችን ጨምሮ ለማስፋፊያ ሥራው አስፈላጊ የሆኑ ዕቃዎች ሳይት ሲደርሱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች እንደሚጀመሩም ተናግረዋል፡፡
የወላይታ ሶዶ ሁለተኛ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የማስፋፊያ ሥራ ከ116 በላይ ለሚሆኑ የአካባቢው ዜጎች ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠሩንም ተናግረዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



