ተቋሙ የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ ነው

ተቋሙ የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያከናውናቸውን የኃይል ማከፋፈያ እና ማስተላለፊያ መስመር ፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለማሻሻል በትኩረት እየሰራ መሆኑን አስታወቀ።

በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ግንባታ ዘርፍ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ክብሮም ካህሳይ እንደገለፁት ተቋሙ በራስ ኃይል እና በውጭ ሥራ ተቋራጮች የኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ጣቢያና የማስተላለፊያ መስመሮችን ግንባታ እያካሄደ ይገኛል።

ፕሮጀክቶቹ የኃይል አቅርቦቱን ተደራሽነት በማሳደግ በኩል ሚናቸው የጎላ በመሆኑ በታቀደላቸው ጥራት፣ ጊዜና በጀት እንዲጠናቀቁ ተቋሙ ጠንካራ ክትትልና ቁጥጥር እያደረገ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

የፕሮጀክቶች የግንባታ ሥራ ሲጀመር በአዋጭነት ጥናቱ ወቅት ያልታዩ ችግሮች እንደሚያጋጥሙ የጠቆሙት አቶ ክብሮም ተቋሙ ከሥራ ተቋራጮችና ከአማካሪዎች ጋር ችግሮችን በጋራ እየገመገመ ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ላይ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

እንደ አቶ ክብሮም ገለፃ የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለማሳደግ ባለሙያዎች ተገቢውን ዕውቀትና ክህሎት እንዲያገኙ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር የተለያዩ ሥልጠናዎች እንዲወስዱ እየተደረገ ነው፡፡

ለፕሮጀክት ሥራ አስኪያጆች በፕሮጀክት አስተዳደር ዙሪያ የአቅም ግንባታ ሥልጠናዎችን በመስጠት ዓለም አቀፍ የብቃት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ መደረጉንም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በአሁኑ ወቅት 40 በመቶ የሚሆኑት የተቋሙ የፕሮጀክት አመራሮች ዓለም አቀፍ የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን የተናገሩት ሥራ አስፈፃሚው ይህም ዓለም አቀፍ ልምዶችንና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ የፕሮጀክቶችን አፈፃፀም ለማሳደግ ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሀገር አቀፍ ደረጃ የፕሮጀክት አስተዳደር ፈተናን ከወሰዱ ተቋማት መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገቡን በመግለፅ ይህም ተቋሙ ተወዳዳሪ የሆኑ የፕሮጀክት አመራሮች እንዳሉት ማሳያ ነውም ብለዋል፡፡

እንደ አቶ ክብሮም ገለፃ ከአቅም ግንባታ ሥራው በተጨማሪ ከውጭ ምንዛሬ፣ ከካሳ ክፍያ፣ ከፅጥታ ችግሮች እና ከስርቆት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በፕሮጀክቶች አፈፃፀም ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ፡፡

እነዚህን ችግሮች ከሚመለከታቸው የመንግስትና የፀጥታ አካላት እንዲሁም ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር መፍትሔ በመስጠት ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ሳይቋረጥ ለመስራት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡

ለፕሮጀክቶች የአሰራር መመሪያዎችን በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ፣ የልምድ ልውውጥ መድረኮችን በመፍጠር እንዲሁም ተገንብተው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያ ልምዶችን በመውሰድ ወጥና የተሻለ የፕሮጀክት አፈፃፀም እንዲኖር እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

በዚህም ከጊዜ ወደ ጊዜ የተቋሙ የፕሮጀክት አፈፃፀም እየተሻሻለ በመምጣቱ ሳቢያ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት ፕሮጀክቶችን የመደገፍ ዝንባሌያቸው እያደገ መምጣቱንም ጠቁመዋል፡፡

ተቋሙ በአሁኑ ወቅት ከ22 በላይ የኃይል ማስተላለፊያ እና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክቶች ግንባታ በመላው የሃገሪቱ ክፍሎች እያከናወነ ይገኛል፡፡

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top