በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ሪጅን በሚያከናውናቸው የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎች ላይ እያጋጠሙ የሚገኙ ችግሮችን ለመፍታት እየተሰራ መሆኑን በተቋሙ የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ የሥራ ኃላፊዎች ከሰሜን ሪጅን የማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና የሥራ መሪዎች እና ሠራተኞች ጋር በሪጅኑ እያጋጠሙ በሚገኙ ችግሮች እና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ውይይት አካሒደዋል፡፡
የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ገ/ እግዚአብሔር በሰሜኑ የሃገሪቱ ክፍል ተከስቶ በነበረው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ጉዳት ደርሶባቸው ለነበሩ የኤሌክትሪክ መሠረተ ልማቶች ዘላቂ መፍትሔ መስጠት ባለመቻሉ፣ የጣቢያዎችን አቅም ለማሳደግና በዕቅድ ተይዘው የቆዩ ፕሮጀክቶች ትግበራ በመዘግየቱ እና የመልሶ ግንባታ ሥራዎች በአፋጣኝ ባለመከናወናቸው በሪጅኑ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ተግዳሮት አንደሆነ በውይይቱ ወቅት አንስተዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ከምዘና ሥርዓት፣ ከዕድገትና ዝውውር፣ ከጥቅማ ጥቅም እና ከሠራተኞች አቅም ግንባታ እንዲሁም ከመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት፣ ከሥራ ላይ ደህንነትና ከሥራ መሳሪያዎች አቅርቦት ጋር የተያያዙ ችግሮች እንደሚስተዋሉ አንስተዋል::
በሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ የማስተላለፊያ መስመሮች ማስተባባሪያ አንድ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መንግሥቱ የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት እጥረት እንደ ተቋም የሚስተዋል ችግር መሆኑን ገልፀው ችግሩን ለመቅረፍም ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዚህም ተቋሙ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ አካላት የመለዋወጫ ዕቃዎችን ከሀገር በቀል አምራቾች ግዥ ለመፈፀም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
የሥራ ላይ መሳሪያዎች ችግርን ለመቅረፍ በ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ግዥ በመፈፀም ለሁሉም ሪጅኖች መከፋፈሉን ያስታወሱት አቶ ተስፋዬ በሪጅኑ ያለውን የሥራ ላይ ደህንነትና የሥራ መሳሪያዎች ዕጥረት በዘላቂነት ለመፍታት በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
በሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ የማስተላለፊያ መስመሮች ማስተባባሪያ ሁለት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀሐይነህ አበበ በበኩላቸው ጉዳት የደረሰባቸውን የማስተላለፊያ መስመሮች መልሶ ለመጠገን 1 ሺ 700 ኪሎ ሜትር የኮንዳክተር ግዥ መፈፀሙን ተናግረዋል።
የኮንዳክተር ገመዶቹ ጥቅም ላይ ከመዋላቸው በፊት ጉዳት የደረሰባቸውን የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች በጥናት በመለየት ወደ ሥራ ለማስገባት ጥረት እንደሚደረግም አብራርተዋል፡፡
በሪጅኑ የሚገኙ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ለማሳደግ እንደሚሰራ የተናገሩት የማከፋፈያ ጣቢያዎች የሪጅን ማስተባበሪያ ሁለት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውዱ አስማረ ዘርፉ የፓወር ትራንስፎርመር፣ የብሬከር እና ሌሎች የመለዋወጫ ዕቃ አቅርቦት ችግሮችን ለመፍታት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የማጠቃለያ ሃሳብ ያነሱት በዘርፉ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ ሁሉም ሠራተኛ ተቋማዊ አስተሳሰብ እንዲኖረው በማድረግ ችግሮችን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



