በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የንብረት አስተዳደርና ጠቅላላ አገልግሎት ዘርፍ በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ ከዘርፉ ሠራተኞችና ከአሽከርካሪዎች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የዘርፉ ሥራ አሥፈጻሚ ወ/ሮ ስመኝ አያሌው እንደገለጹት ውይይቱ በ2017 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የዘርፉ ሠራተኞችና የሥራ መሬዎች የጋራ መረዳት ኖሯቸው ተቀናጅተው ለተሻለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ለማድረግ ነው።
በዘርፉ ለሠራተኛው ምቹ የሥራ ከባቢ ከመፍጠር፣ የተቋሙን ንብረቶችን ከማስተዳደር፣ የጥገና ሥራዎችን ከማከናወን እና የሰርቪስ ተሽከርካሪዎችን ከማቅረብ አኳያ በ2016 በጀት ዓመት በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን አስታውሰዋል።
ኃላፊዋ አክለውም አገልግሎት የማይሰጡ ንብረቶችን ከማስወገድ፣ የቆዩ የተቋሙ ሠነዶችን ከማደራጀት፣ ምቹ የሥራ ከባቢን ከመፍጠር እና ለሠራተኞች የሰረቪስ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር አበረታች ሥራዎች ተከናውነዋል ብለዋል።
ሆኖም በየመጋዘኖቹ ተገዝተው የሚገቡ ብዛት ያላቸው የተለያዩ የሥራ ክፍል ዕቃዎች ቶሎ ያለመውጣት፣ ከፍተኛ የቦታ ጥበት፣ በዕቃ ግምጃ ቤት ቅጥር ግቢ የኢንተርኔት ችግር መኖር፣ የአንዳንድ ዕቃዎች መመዘኛ መስፈርት ማግኘት አለመቻል፣ የስቶር ግንባታው በታቀደለት ጊዜ አለመጠናቀቅ፣ የመለዋወጫ ችግር እና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ የማስወጣት ሥራ በዕቅዱ መሠረት አለመፈጸም ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸው ተገልጿል።
እንደ ሥራ አስፈጻሚዋ ገለጻ በ2016 በጀት ዓመት የተከናወኑ ሥራዎች ለ2017 በጀት ዓመት እቅድ መደላድል የፈጠረ መሆኑን አስታውሰዋል።
በ2017 በጀት ዓመት የተቋሙን ንብረት አያያዝና አጠቃቀም መመሪያ አውጥቶ ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሰራ የተናገሩት ወ/ሮ ስመኝ 600 ለሚሆኑ የተቋሙ ተሽከርካሪዎች ጂፒኤስ መገጠሙንና በዚህ ዓመት ሥራ ላይ እንደሚውል ጠቁመዋል።
ሥራ አስፈጻሚዋ አክለውም ተቋሙ ያሉት ተሽከርካሪዎችን በአግባቡ ተጠግነው ሥራ ላይ እንዲውሉ የመካከለኛ ጋራዥ በዚሁ በጀት ዓመት ግንባታው እንደሚጀመር ገልጸዋል።
ከመለዋወጫ እቃ እጥረት፣ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጋር ያለው የይዞታና ንብረቶች ጉዳይ በዘላቂነት ለመፍታት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ ተናግረዋል።
በውይይቱ ላይ የመምሪያ ኃላፊዎች የ2017 በጀት ዓመት ዕቅዳቸውን አቅርበው ከተሳታፊዎች ጥያቄዎችና አስተያየቶች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



