በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ከሰሜን ሪጅን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በሪጅኑ እየተከናወኑ ስላሉ ሥራዎች እና ተግዳሮቶች ዙሪያ በመቐለ ከተማ ውይይት እያካሄደ ይገኛል።
በውይይቱ ላይ የተገኙት በዘርፉ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንደተናገሩት ውይይቱ ሪጅኑ በሚያከናውናቸው ሥራዎች ላይ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ላይ ውይይት በማድረግ የቀጣይ የሥራ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ያለመ ነው።
ከዚህ በተጨማሪም የሪጅኑ ሠራተኞች በአካባቢው የነበረውን ችግር ተቋቁመው ላከናወኑት ሥራ በዘርፉ እውቅና ለመስጠት ዓላማ ያደረገ እንደሆነም አመላክተዋል።
ከሪጅኑ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር እየተካሄደ ያለው ውይይት ሪጅኑ ድጋፍ የሚፈልግበትን ጉዳዮች ግብዓት በመሰብሰብ በቀጣይ ለጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደሚያግዝም አቶ ጋሻው ተናግረዋል።
የሰሜን ሪጅን ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሮቤል ገ/ እግዚአብሔር በበኩላቸው ውይይቱ በሪጅኑ የሚነሱ የተለያዩ ችግሮችን በመውሰድ እልባት ለመስጠት ያስችላል ብለዋል።
መስከረም 20 እና 21 ቀን 2017 ዓ.ም በሚካሄደው ውይይት ላይ የሪጅኑ የማከፋፈያ ጣቢያዎች፣ የማስተላለፊያ መስመርና የፋይበር ኦፕቲክስ የኦፕሬሽንና ጥገና ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንዲሁም በሪጅኑ ስር የሚገኙ የማከፋፈያ ጣቢያ ኃላፊዎች እንደሚሳተፉበት አቶ ሮቤል ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ውይይቱ ከኃይል ማስተላለፊያ መስመር የኦፕሬሽንና ጥገና ሠራተኞች ጋር በመካሄድ ላይ የሚገኝ ሲሆን ከሰዓት በኋላም ከማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽንና የጥገና ሠራተኞች ጋር የሚቀጥል ይሆናል።
ከውይይቱ በተጨማሪ በሪጅኑ በሚገኙ አንዳንድ ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ ጉብኝት እንደሚካሄድ ከመርሃ ግብሩ ለመረዳት ተችሏል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

