ማመንጫ ጣቢያው በበጀት ዓመቱ 296 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማመንጨት አቅዷል

ማመንጫ ጣቢያው በበጀት ዓመቱ 296 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ለማመንጨት አቅዷል

የአይሻ 2 የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያ በተያዘው የ2017 በጀት ዓመት 296 ጊጋ ዋት ሰዓት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት ማቀዱን የጣቢያው የኦፕሬሽን ሥራ አስኪያጅ ገለፁ፡፡

ሥራ አስኪያጁ አቶ ታረቀኝ ተመስገን እንደገለፁት ጣቢያው በ2016 በጀት ዓመት 175 ጊጋ ዋት ሰዓት ለማምረት አቅዶ 125 ጊጋ ዋት ሰዓት ኃይል ማመንጨት ችሏል።

የ2017 በጀት ዓመት ዕቅዱን ለማሳካትና መደበኛ የኦፕሬሽን ሥራውን አስተማማኝ ለማድረግ ከፕሮጀክት ቢሮ እና ሥራ ተቋራጩ ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም አቶ ታረቀኝ ገልፀዋል።

የኃይል ማመንጫ ጣቢያው በግንባታ ሂደት ላይ ሆኖ ኤሌክትሪክ ማመንጨት መጀመሩ ተጨማሪ ኢነርጂ ወደ ብሔራዊ ኃይል ቋት እንዲገባ ዕድል ፈጥሯል ብለዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በጣቢያው ከተተከሉት 32 የንፋስ ተርባይኖች ውስጥ በአሁኑ ወቅት 23ቱ ኃይል በማመንጨት ላይ ይገኛሉ።

በተያዘው በጀት ዓመት በፍተሻና ሙከራ ላይ የሚገኙ 8 ተርባይኖችን በመረከብና ወደ ኦፕሬሽን በማስገባት ኃይል የሚያመነጩትን የንፋስ ተርባይኖች ቁጥር ወደ 31 ከፍ ለማድረግ ይሰራልም ብለዋል።

የኃይል ማመንጫው የጥገናና የኦፕሬሽን ሥራዎች ከፕሮጀክቱ ባለሙያዎች ጋር በጥምረት እየተከናወነ በመሆኑ የዕውቀት ሽግግሩ በከፍተኛ ሁኔታ እያገዛቸው እንደሚገኝ አቶ ታረቀኝ ጠቅሰዋል።

ለጣቢያው የኦፕሬሽን ሠራተኞች እየተገነቡ የሚገኙት መኖሪያ ቤቶች በጥራትና በፍጥነት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ ለማድረግ ከፕሮጀክት ቢሮው ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝም ገልፀዋል።

በኃይል ማመንጫው አካባቢ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በአስተዳደር ክፍሉ አማካኝነት ተደጋጋሚ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች መከናወናቸውን አቶ ታረቀኝ ተናግረዋል።

120 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም ያለው የአይሻ ሁለት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በኢትዮጵያ መንግስትና ከቻይና ኤግዚም ባንክ በተገኘ 270 ሚሊየን ዶላር እየተገነባ የሚገኝ ፕሮጀክት ነው።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top