የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

የማከፋፈያ ጣቢያውን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

በድሬዳዋ ቁጥር ሦስት ባለ 230/132/33/15 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የመቆጣጠሪያ ክፍል የአቅም ማሳደግና ማሻሻል ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የጣቢያው ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

ሥራ አስኪያጁ አቶ አበባው አበራ እንደገለፁት እየተከናወነ የሚገኘው የአቅም ማሳደግና የማሻሻያ ሥራ የማከፋፈያ ጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራዎች ለማዘመን የሚያግዝ ነው።

የአቅም ማሳደግና የማሻሻያ ሥራው በማከፋፈያ ጣቢያው ለረጅም ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ የቆዩትን መቆጣጠሪያዎች በሌላ ዘመናዊ የመቆጣጠሪያ መሳሪያ ለመቀየር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ አበባው እንደገለፁት ቀደም ሲል የነበረው የጣቢያው መቆጣጠሪያ በአየር የሚሰራ (vacume switchgear ) ሲሆን በአሁኑ ወቅት ሊቀየር በሂደት ላይ የሚገኘው መቆጣጠሪያ ደግሞ በጋዝ የሚሰራ ጂ.አይ.ኤስ (Gas Insulated System) ነው፡፡

በአየር የሚሰራው መቆጣጠሪያ የኃይል መቋረጥ ችግሮች ሲያጋጥሙ የጥገና ሥራ በተቀላጠፈ መልኩ ለማከናወን አስቸጋሪ ሁኔታዎች እንደሚፈጠሩ አቶ አበባው አስታውሰዋል።

የመቆጣጠሪያው መቀየር የኃይል መቆራረጥንና በጥገና ሥራዎች ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ የመዘግየት ችግሮችን በመቅረፍ የኦፕሬሽንና የጥገና ሥራዎችን በቀላሉ ለማከናወን እንደሚረዳም ነው ሥራ አስኪያጁ የጠቆሙት።

በአሁኑ ወቅት ለብሬከር ቅየራ ሥራው የሚያስፈልጉ የሲቪል ሥራዎች መጠናቀቃቸውን ያብራሩት አቶ አበባው የጂ.አይ.ኤስ ተከላ ሥራውን በሪጅኑና ከዋና መስሪያ ቤት በተውጣጡ የቴክኒክ ባለሙያዎች ጥምረት ለማከናወን እየተሰራ ይገኛልም ብለዋል።

የማሻሻያ ሥራው በዋናነት በ33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ላይ እየተከናወነ እንደሚገኝ ያነሱት አቶ አበባው ይህም የጣቢያውን የኦፕሬሽን ሥራዎች ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ ለማከናወን ያስችላል ብለዋል።

የ15 እና 33 ኪሎ ቮልት መቆጣጠሪያዎች ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ በመቆየታቸው ለኃይል መቆራረጥ ምክንያት እየሆኑ እንደሚገኙ አንስተዋል።

እንደ ሥራ አስኪያጁ ገለፃ በጣቢያው በ33 ኪሎ ቮልት ሦስት ወጪ መስመሮች የሚገኙ ሲሆን መስመሮቹም ለቱሬ ሲሚንቶ፣ ለፓዮኔር ሲሚንቶ እና ለሸሙ የሳሙና ፋብሪካ እንዲሁም ለሐረር የንፁህ መጠጥ ውሃ መስመር ኃይል እያቀረቡ ይገኛሉ።

በ15 ኪሎ ቮልት አንድ ወጪ መስመር እንደሚገኝ የጠቀሱት አቶ አበባው መስመሩም ለመልካ ጀብዱ፣ ኩባ ካምፕና ለማረሚያ ቤት ኃይል እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የተጀመረውን የ33 ኪሎ ቮልት የዘመናዊ ብሬከር ቅየራ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ዝግጁ ለማድረግ እየተሰራ ይገኛል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top