ተቋሙ ምቹና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን በማቅረብ የሠራተኞችን እርካታ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው

ተቋሙ ምቹና ዘመናዊ ተሽከርካሪዎችን በማቅረብ የሠራተኞችን እርካታ ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለሠራተኞቹ ምቹና ዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎችን በማቅረብ የሥራ ላይ እርካታቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ አስታወቀ።

ተቋሙ ከ215 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከበላይነህ ክንዴ ግሩፕ የገዛቸውንና በዋናው መስሪያ ቤት ለሚገኙ ሠራተኞች የሰርቪስ አገልግሎት የሚሰጡ በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች ግዢ መፈፀሙን የንብረትና ጠቅላላ አገልግሎት ዘርፍ ገልጿል።

የዘርፉ ተወካይ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ከሊል ሺፋ እንደገለፁት ተቋሙ በአሁኑ ወቅት በ22 የተለያዩ መስመሮች ለሠራተኞች የሰርቪስ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 14ቱ ተሽከርካሪዎች የኪራይ ናቸው።

በዚህም ተቋሙ ለሰርቪስ ኪራይ በወር ከ1 ሚሊየን እንዲሁም ለነዳጅና ለተለያዩ የጥገና ሥራዎች ከ1 ነጥብ 6 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እያደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ ግዢ ለተቋሙ ወጭ ቅነሳ ከፍተኛ ፋይዳ እንደሚኖራቸው ያነሱት አቶ ከሊል የትራንስፖርት አገልግሎት ለማሟላት እየተደረገ ያለው ጥረት ሠራተኛው ተረጋግቶ ሥራውን እንዲያከናውን እንደሚያግዘው ተናግረዋል።

ተቋሙ ከኩባንያው ለመግዛት ሥምምነት ካደረገባቸው 12 የኤሌክትሪክ ተሸከርካሪዎች መካከል አራት አውቶብሶችንና 5 መካከለኛ አውቶብሶችን የተረከበ ሲሆን በቀጣይም አንድ መካከለኛ አውቶብስና ሁለት ሚኒባሶችን እንደሚረከብ ገልፀዋል።

የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹን ለሚረከቡ ሹፌሮች በኩባንያው በኩል ተጨማሪ የቴክኒክና ተያያዥ ሥልጠናዎች እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

ለኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎቹ የቻርጅ ማድረጊያ ጣቢያ ቦታ መረጣ ተከናውኖ ቻርጀሮቹ የሚቀመጡበት የመሰረት ሥራ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ ከሊል ጣቢያው በሚኖሩት ሁለት የቻርጅ ማድረጊያ መሳሪያዎች 4 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ በ45 ደቂቃ ውስጥ ለመሙላት የሚያስችል አቅም እንዳለውም ነው ያብራሩት።

ተቋሙ በሀገር ውስጥ የተገጣጠሙ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ግዥ መፈፀሙ ከግዥ በኋላ የሚካሄዱ የጥገና ሥራዎችን በአምራቹ በኩል እንዲከናወኑ በማድረግ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በወቅቱ ለመፍታት ያግዛል ብለዋል።

እንደ አቶ ከሊል ገለፃ በቀጣይ ለተቋሙ ሥራ የሚያገለግሉ አነስተኛና መለስተኛ ተሸከርካሪዎችን በኤሌክትሪክ በሚሰሩ ተሸከርካሪዎች ለመቀየር ዝግጅት እየተደረገም ይገኛል።

? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top