የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ለአራት ወራት በኤሌክትሮ መካኒካል የትምህርት ዘርፍ ያሰለጠናቸውን 44 ቴክኒሺያኖች በዛሬው ዕለት አስመርቋል።
የተቋሙን ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመወከል በምረቃ ሥነ- ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን እንደተናገሩት ተቋሙን በአህጉርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪና አስተማማኝ የኃይል አቅራቢ ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ፡፡
የተቋሙን ርዕይ ለማሳካት የሥልጠና ማዕከሉን ውጤታማ የሚያደርግ የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ስትራቴጅ ተነድፎ እየተሰራ እንደሆነ አንስተዋል፡፡
በዕውቀት፣ በክህሎት እና በአመለካከት የዳበረ ሠራተኛ ለመፍጠር የማሰልጠኛ ማዕከሉን በአሰራር፣ በግብዓት እና በአደረጃጀት የማዘመን ሥራ ተጠናክሮ እንደሚከናወን አቶ ሞገስ አረጋግጠዋል፡፡
በተቋሙ የሰው ሀብት ልማት መምሪያ ዳይሬክተር ወንድወሰን ካሳ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኤሌክትሮ መካኒካል ሥልጠናው ሠልጣኞች ወደ ሥራ ዓለም ከመግባታቸው በፊት ስለ ተቋሙና ስለሚያከናውኑት ሥራ በቂ ግንዛቤ የሚያስይዝ ነው ብለዋል፡፡
በሥልጠናው ይዘትና አሰጣጥ ላይ ማሻሻያዎችን በማድረግ ከሠልጣኞች የአመለካከት ለውጥ ጋር የተያያዙ ባህሪያዊ ሥልጠናዎች መካተታቸውንም አመልክተዋል፡፡
በሥልጠናው ላይ ከታዳጊ ክልሎች እንዲሁም በተለያየ ምክንያት የሰው ኃይል ካልተሟሉባቸው የሥራ አካባቢዎች በልዩ ሁኔታ ሠልጣኞች እንዲመለመሉ መደረጉንም አንስተዋል፡፡
በተቋሙ የሠው ኃይል ሥራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ ተማም አፍደል በበኩላቸው ተቋሙ የሶስት ዓመት ግሪድ ስትራቴጅ በመቅረጽ ወደ ተግባር መግባቱን በማስታወስ ዕቅዱን ለማሳካት የዛሬ ተመራቂዎች ድርሻቸው የጎላ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ተመራቂዎቹ በኦፕሬሽን ዘርፎች ላይ የሚስተዋለውን የሰው ኃይል ፍላጎት ክፍተት ለማሟላት ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱም ጠቁመዋል፡፡
በተቋሙ የስልጠናና ልማት ማዕከል ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምስ ሰይፉ የሥልጠና ማዕከሉ ተቋሙ እንደ አዲስ ከተቋቋመበት ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ 800 የሚሆኑ ሠልጣኞችን በዘርፉ በማሰልጠን በኦፕሬሽን የሥራ ዘርፎች ላይ እንዲሳተፉ ማድረጉን አስታውቀዋል፡፡
በተያዘው በጀት ዓመት ማዕከሉ 39 ወንድና 5 ሴት ሠልጣኖችን በኤሌክትሮ ሜካኒካል የትምህርት ዘርፍ ማስመረቁን ተናግረዋል፡፡
ለምረቃ ከበቁት ሰልጣኞች መካከል አስሩ ከአርብቶ አደር አካባቢ የመጡ መሆናቸውን የገለፁት ሥራ አስኪያጁ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የማደሪያ ቦታ፣ የኪስ ገንዘብ፣ የትራንስፖርትና የውሃ አቅርቦት እንደተመቻችላቸው ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ደምስ ገለፃ ተመራቂዎቹ በስልጠና ቆይታቸው ከሥራው ጋር ግንኙነት ያላቸው ኮርሶችን በንድፈ ሃሳብና በተግባር በተደገፈ መልኩ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ልምድ ባላቸው የተቋሙ ሠራተኞች ወስደዋል፡፡
በማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እና የተቋሙ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ፀሐፊ አቶ ኃይሉ ወልዴ በፕሮግራሙ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ተመራቂዎቹ ተቋሙ የነደፈውን ስትራቴጅ ለማሳካት ከፍተኛ አደራ እንደተጣለባቸው ተገንዝበው ለተቋሙ ምርታማነት የበኩላቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡
ተመራቂዎቹ በሚሰማሩበት የሥራ መስክ የሚሰጣቸውን ኃላፊነት ሙያዊ ስነ-ምግባርን በተላበሰና የሙያ ደህንነትን ባከበረ መልኩ በትጋትና በቅንነት ተቋሙን እንደሚያገለግሉ ቃል ገብተዋል።
በዕለቱም የላቀ ውጤት ላስመዘገቡ ተመራቂዎች እና ለመምህራን የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”









