በደቡብ አንድ ሪጅን ሥር በሚገኙ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚሰራ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ አስታወቀ።
በዘርፉ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ከደቡብ አንድ ሪጅን የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በሐዋሳ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
ውይይቱ በሪጅኑ እየተከናወኑ ስለሚገኙ የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎች እንዲሁም በሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሔዎቻቸው ዙሪያ ላይ ትኩረቱን አድርጓል።
በዘርፉ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እንድሪያስ እንደገለፁት ውይይቱ ሪጅኑ በሚያከናውናቸው የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎች ላይ እያጋጠሙ የሚገኙ ችግሮችን በመለየት የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያግዛል።
ሪጅኖች የሚያስፈልጓቸውን ድጋፎች ለይቶ ለማቅረብ፣ የቁጥጥርና ግምገማ ሥራዎችን ለማከናወን፣ የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎችን ለመከታተልና ኦዲት ለማድረግ መምሪያው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ከሪጅኑ የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ጋር በተካሄደው ውይይት ሪጅኑ ድጋፍ በሚፈልግባቸው ጉዳዮች ላይ ግብዓት በመሰብሰብ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እንደሚረዳም ነው አቶ ጋሻው የጠቀሱት።
የደቡብ አንድ ሪጅን ማስተላለፊያ መስመሮች እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ንጉሴ በበኩላቸው ውይይቱ የሪጅኑን የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎች ለማሻሻል ያግዛል ብለዋል።
በሪጅኑ 12 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ጠቅሰው አብዛኞቹ ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት እየሰጡ በመቆየታቸው የአቅም ማሳደግና ማሻሻያ ሥራዎች እንደሚያስፈልጋቸው ገልፀዋል።
እንደ አቶ ምትኩ ገለፃ ሪጅኑ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ማቅረብ እንዲችል በኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ብረቶች ላይ በተደጋጋሚ እየተፈፀመ ያለውን ስርቆት ማስቆም ይገባል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የፍተሻና ቁጥጥር ሥራዎችን ለማከናወን የካሳ ይገባኛል ጥያቄዎች ችግር እየፈጠሩ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።
ከምዘና ሥርዓት፣ ከዕድገትና ዝውውር፣ ከሠራተኞች አቅም ግንባታና ከኃይል ተሸካሚ ምሰሶ ስርቆት ጋር በተያያዘ የሚስተዋሉ ችግሮችን መፍታት እንደሚገባም አሳስበዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



