የደቡብ አንድ ሪጅን የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሥራ ኃላፊዎችና የጥገና ሠራተኞች ለኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎች ማነቆ የሆኑ ችግሮች እንዲፈቱ ጠየቁ።
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ኦፕሬሽን ዘርፍ የሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ የሥራ ኃላፊዎች ከደቡብ አንድ ሪጅን የሥራ ኃላፊዎችና የጥገና ሠራተኞች ጋር በሐዋሳ ከተማ ውይይት አካሂዷል።
የሪጅኑ የኃይል ማስተላለፊያና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሥራ ኃላፊዎችና የጥገና ሠራተኞች በውይይቱ ወቅት እንደገለፁት በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ የብረት ምሰሶዎች ላይ እየተፈፀመ ያለው የስርቆት ወንጀል አሳሳቢነቱ ጨምሯል።
የስርቆት ወንጀሉ ከጊዜ ወደ ጊዜ መልክና ይዘቱን እየቀየረ መምጣቱን የጠቀሱት የጥገና ሠራተኞቹ ይህም የመለዋወጫ ዕቃዎች እጥረት እንዲያጋጥምና ተደጋጋሚ የኃይል መቋረጦች እንዲከሰቱ ምክንያት ሆኗል ብለዋል።
በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮች ላይ የፍተሻና ቁጥጥር ሥራዎችን ለማከናወን የካሳ ይገባኛል ጥያቄዎች ማነቆ እየሆኑባቸው መምጣታቸውን የገለፁት ባለሙያዎቹ ተቋሙ ከክልል፣ ዞንና ወረዳ አመራሮች እንዲሁም ከፀጥታ አካላት ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩ መፍትሔ የሚያገኝበትን አሰራር እንዲዘረጋ ጠይቀዋል።
በሪጅኑ የሚገኙ አብዛኞቹ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ለበርካታ ዓመታት አገልግሎት ሲሰጡ በመቆየታቸው ሳቢያ የመለዋወጫ ዕቃዎች፣ የሥራ ላይ ደህንነት መጠበቂያ እና የቻርጀርና ባትሪ እንዲሁም የዘይት መፈተሻ መሳሪያዎች አቅርቦት እጥረት እንዳለባቸው ነው የውይይቱ ተሳታፊዎች ያብራሩት።
በሪጅኑ ከትምህርትና ሥልጠና፣ ከተሽከርካሪ አቅርቦት እና ከሰው ኃይል አደረጃጀት እንዲሁም ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቶችን ተግባራዊ ከማድረግ አንፃር ክፍተቶች እንደሚስተዋሉም ጠቅሰዋል።
በሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ የማስተላለፊያ መስመሮች ማስተባበሪያ አንድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ተስፋዬ መንግሥቱ እንደገለፁት እንደ ተቋም የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት እየተሰራ ነው።
ተቋሙ የኃይል ተሸካሚ ምሰሶ አካላት የመለዋወጫ ዕቃዎችን ከሀገር በቀል አምራቾች ግዥ ለመፈፀም በሒደት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
1 ሺህ 700 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የኮንዳክተር ሽቦ ገመድ ግዥ መፈፀሙን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ በ1 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተገዙ የሥራ ላይ መሳሪያዎችም ለሁሉም ሪጅኖች መከፋፈላቸውን ተናግረዋል።
የሥራ ላይ ደህንነት መሳሪያዎች ለሁሉም የጥገና ባለሙያዎች መሟላት እንዳለባቸው የጠቆሙት አቶ ተስፋዬ ሠራተኞች በጥገና ወቅት ከሥጋት ቀጠና ራሳቸውን ጠብቀው የሚሰሩበትን መንገድ ለማመቻቸት ትኩረት መደረግ እንዳለበት ገልፀዋል።
በሪጅኖች ማስተባበሪያ መምሪያ የማከፋፈያ ጣቢያዎች ማስተባበሪያ አንድ ሥራ አስኪያጅ አቶ ፀጋዬ ጌታሁን በበኩላቸው የጥገና ሠራተኞች በኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሚስተዋሉ ችግሮችን ለይቶ ለመፍትሔው በጋራ መስራት አለባቸው።
የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን አቅም ለማሳደግ የሚያስችሉ ሥራዎች መጀመራቸውን ያነሱት ሥራ አስኪያጁ ከዚህ ጋር ተያይዞ እያጋጠሙ የሚገኙ የመለዋወጫ ዕቃዎች አቅርቦት ችግሮችን ለመቅረፍም የተለያዩ ግዥዎች እየተፈፀሙ እንደሚገኙም አብራርተዋል።
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”




