የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በክልሉ የሚያልፉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ከሚሸከሙ የብረት ምሰሶዎች ላይ አንዲትም ብረት እንዳትሰረቅ ክልሉ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋገጡ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥራ ኃላፊዎች ጋር በስርቆት፣ በወሰን ማስከበር እና ከቢሮ ግንባታ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ውይይት አድርገዋል፡፡
የተቋሙ የኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሸን መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን ለርዕሰ መስተዳድሩ እንዳብራሩት ተቋሙ በ2016 በጀት ዓመት በስርቆትና የተሰረቁ የኃይል መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት ከአንድ ቢሊየን ብር የሚበልጥ ጉዳት ደርሶበታል፡፡
ከዚህ ውስጥ 13 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የሚገመተው በሲዳማ ክልል የተፈፀመ ስርቆት በመሆኑ የክልሉ መንግስት እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር ድርጊቱን ለመከላከል ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡
በፓወር ሪፎርም ኢንቨስትመንት እና ሞደርናይዜሽን ፕሮግራም (PRIME) ከሚገነቡት ማከፋፈያ ጣቢያዎች መካከል የበንሳ ዳዬ ማከፋፈያ ጣቢያ የሚያርፍበትን ቦታ በአዋጅ ቁጥር 1336/2016 መሰረት ተነሺዎችን የመለየት፣ ካሳ የመክፈልና መልሶ የማቋቋም ሥራዎች ከወዲሁ እንዲጀመሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
እንደ አቶ ሞገስ ገለፃ የልማት ተነሺዎች የፕሮጀክቱ ፋይናንስ አቅራቢ የዓለም ባንክ በሚያስቀምጠው የመልሶ ማቋቋም መስፈርት መሰረት ቀድሞ ከነበሩበት ህይወት በተሻለ መንገድ መልሶ ለማቋቋም ትኩረት ሊደረግ ይገባል፡፡
ለሪጅኑ ቢሮ መገንቢያ የሚሆን ቦታ ለማግኘት ከ2012 ዓ.ም. ጀምሮ ሲቀርብ የቆየው ጥያቄ እንዲፈፀምም አቅጣጫ እንዲሰጥበት አመልክተዋል፡፡
በኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የኦፕሬሽን ዘርፍ የደቡብ አንድ ሪጅን ዳይሬክተር አቶ ምትኩ ንጉሴ በበኩላቸው ስርቆቱ በክልሉ በሰሜን ሲዳማ ዞን ብላቴ ዙሪያ ወረዳ ዲን አኖሌ እና ቦሩ ሸወላ ቀበሌዎች በተደጋጋሚ እንደሚፈፀም ተናግረዋል፡፡
በማዕከላዊ ዞን ከይርጋለም – ሻኪሶ በተዘረጋው መስመር ላይም ዳሌ ወረዳ ቤራ ጫሌ እና ዊጮ ቀበሌዎች፤ ከይርጋለም – ዲላ በተዘረጋው መስመር ላይ ደግሞ አዋዳ እና አለታ ጩት ቀበሌዎች እንዲሁም በደቡባዊ ዞን ሳፋ እና ሚሊኒየም ቀበሌዎች ስርቆቱ በስፋት እንደሚስተዋል አንስተዋል፡፡
የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ደስታ ሌዳሞ በሰጡት ምላሽ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሚያከናውናቸው ሥራዎች ህብረሰተባችንን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመሆናቸው ከተቋሙ ጋር ተባብሮ መሥራት የግድ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ስርቆት ማህበረሰቡን በማሳተፍ ለመከላከል በሚከናወነው ሥራ የቅድሚያ ትኩረት ሰጥተው እንደሚከታተሉትና በየደረጃው ለሚገኙ አመራሮች መመሪያ እንደሚሰጡ አስረድተዋል፡፡
በክልሉ የሚያልፉ የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን ከሚሸከሙ የብረት ምሰሶዎች አንዲትም ብረት እንዳትሰረቅ እስከ ቀበሌ ባለው መዋቅር በትኩረት እንደሚሰራም አረጋግጠዋል፡፡
ወደፊት ከሚገነባው የበንሳ ዳዬ ማከፋፈያ ጣቢያ ይዞታ ጋር በተያያዘ የሚያስፈልገውን የካሳ ክፍያ እና ተነሺዎችን መልሶ የማቋቋም ሥራ የአዋጁን መንፈስ ተረድቶ ለመተግበር ውይይት ማድረግና መመካከር እንደሚፈልግ ጠቁመዋል፡፡
የቢሮ መገንቢያ ቦታን በተመለከተም የሐዋሳ ከተማን ደረጃ በሚመጥን መልኩ ጥያቄው ምላሽ የሚያገኝበት ሁኔታ ይመቻቻል ብለዋል፡፡
? “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”



