ፕሮጀክቱን በተያዘው በጀት ዓመት አጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራ ነው

ፕሮጀክቱን በተያዘው በጀት ዓመት አጠናቆ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማድረግ እየተሰራ ነው

የደሴ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ የግንባታ ሥራን በተያዘው በጀት ዓመት አጠናቆ አገልግሎት ለማስጀመር ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የፕሮጀክቱ የሳይት ሥራ አስኪያጅ አስታወቁ።

‎ሥራ አስኪያጁ አቶ አብዲ ኪያር እንዳስታወቁት የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀም 32 በመቶ ደርሷል።

‎በአሁኑ ወቅት የኦፕሬተሮች መኖሪያ፣ የጀነሬተር እና የመቆጣጠሪያ ቤቶች እንዲሁም የስዊችያርድ የመሠረት ግንባታ ሥራ በመከናወን ላይ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።

‎የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ በዕቅዱ መሠረት እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት አቶ አብዲ የፋይናንስ እና የማሽነሪ እጥረቶችን መቅረፍ ከተቻለ ጣቢያው በበጀቱ ዓመቱ ማጠናቀቂያ ላይ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀምር አረጋግጠዋል።

‎ለፕሮጀክቱ ግንባታ መፋጠን የከተማው አስተዳደር የተለያዩ እገዛዎችን እያደረገ እንደሚገኝ የገለፁት የሳይት ሥራ አስኪያጁ ይሁን እንጂ ከዋናው መንገድ ጋር የሚያገናኙ የውስጥ ለውስጥ መንገዶች ግንባታ ለማከናወን የሚያስችል የቦታ ፈቃድ እስካሁን ማግኘት እንዳልተቻለ አብራርተዋል።

‎በፕሮጀክቱ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ሥራዎች ባለሙያ አቶ ዘለቀ አድነው እንደተናገሩት 63 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመጫን አቅም ያላቸው ሁለት ትራንስፎርመሮችን የማስቀመጥ ሥራ ተሰርቷል።

ትራንፎርመሮቹ 104 ሜጋ ዋት ኃይል የመጫን አቅም እንዳላቸው የገለፁት ባለሙያው ይህም ጣቢያው በደሴ እና አካባቢው ለዘመናት ለቆየው የኤሌክትሪክ ፍላጎት ጥያቄ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑን አመልክተዋል።

‎ፕሮጀክቱ ከኮምቦልቻ-አላማጣ ከሚሄደው መስመር ላይ ኃይል ተቀብሎ በስምንት ባለ 15 እና በስምንት ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች ለደሴ ከተማ እና አካባቢው ኤሌክትሪክ ለማቅረብ እየተገነባ እንደሚገኝም ነው የተናገሩት።

‎በአሁኑ ወቅት የ15 ኪሎ ቮልት የጂ.አይ.ኤስ ስዊችጊር ዕቃዎች ተጓጉዘው ሳይት መድረሳቸውን ገልፀው በቀጣይም ቀሪ የ33 ኪሎ ቮልት የስዊችጊር ዕቃዎችን ለማጓጓዝ የሚያስችሉ ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

‎እንደ አቶ አድነው ገለፃ የተለያዩ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችን ለማስቀመጥ የሚረዱ የመሠረትና የገጠማ ሥራዎች በፍጥነት በመከናወን ላይ ናቸው።

‎የደሴ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኢንጅነሪንግ እና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ ዘርፍ እየተከናወነ ሲሆን ሲዋን የተሰኘ የቻይና ኩባንያ ደግሞ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎችን በማቅረብ እየተሳተፈ ይገኛል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top