በጣቢያው ትራንስፎርመር ላይ የተከናወነው የጥገና ሥራ የተቋሙን ባለሙያዎች አቅም ያሳየ ነው

በጣቢያው ትራንስፎርመር ላይ የተከናወነው የጥገና ሥራ የተቋሙን ባለሙያዎች አቅም ያሳየ ነው

በኮምቦልቻ አንድ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፊያ ጣቢያ ትራንስፎርመር ላይ የተከናወነው የጥገና ሥራ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሙያዎችን አቅም ያሳየ መሆኑን የሰሜን ምስራቅ 1 ሪጅን አስታወቀ።

‎በሪጅኑ የኦፕሬሽንና ጥገና መምሪያ ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ደስታዬ ስጦታው እንደገለፁት የጥገና ሥራው የተከናወነው ጣቢያው ካሉት ሁለት ትራንስፎርመሮች መካከል በአንደኛው ላይ የእሳት አደጋ በማጋጠሙ ምክንያት ነው።

‎40 ሜጋ ቮልት አምፒር ኃይል የመጫን አቅም ባለው ትራንስፎርመር ታፕ ቸንጀር ላይ ጉዳት በመድረሱ ሳቢያ በደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞች ለአንድ ወር ያህል በከፊል የኃይል መቋረጥ አጋጥሞ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

‎ጉዳት የደረሰበትን ትራንስፎርመር በአስቸኳይ ጠግኖ ዳግም ወደ አገልግሎት እንዲመለስ ለማድረግ ከሪጅኑ እና ከዋና መስሪያ ቤት የተውጣጡ ባለሙያዎች ሲሳተፉ መቆየታቸውንም ነው የተናገሩት።

‎በጣቢያው አንደኛው ትራንስፎርመር ላይ የተከናወነው የጥገና ሥራ በሪጅኑ ታሪክ የመጀመሪያ መሆኑን የጠቆሙት ተወካይ ዳይሬክተሩ ጉዳት የደረሰበትን ትራንስፎርመር የላይኛውን ሽፋን በማንሳት ስኬታማ ሥራ መሰራቱን አብራርተዋል።



‎በወቅቱ የኃይል መቋረጥ አጋጥሟቸው ለነበሩ ከተሞች በአፋጣኝ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ የሚያስችሉ የተለያዩ ሥራዎች ሲከናወኑ እንደነበረ የገለፁት አቶ ደስታዬ ከኮምቦልቻ ቁጥር ሁለት ማከፋፈያ ጣቢያ ኃይል በመስጠት ችግሩን በከፊል መቅረፍ መቻሉን ጠቅሰዋል።

‎የሪጅኑ የጥገና ባለሙያዎች ያላቸውን አቅም ይበልጥ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል የተለያዩ ሥልጠናዎች በዙር እንዲያገኙ እየተደረገም ነው ብለዋል።

‎እንደ አቶ ደስታዬ ገለፃ ሪጅኑ በሚያስተዳድራቸው ሌሎች የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ላይ መሰል ችግሮች እንዳይከሰቱ ለማድረግ የቁጥጥርና ክትትል ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

‎በአሁኑ ወቅት በከፊል ተቋርጦ የቆየው ኃይል ሙሉ በሙሉ መመለሱን ገልፀው በጥገና ሥራው ላይ ርብርብ ሲያደርጉ ለነበሩ የጥገና ባለሙያዎች በሙሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

‎የኮምቦልቻ አንድ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ደምስ ሳህለ ማሪያም እንደተናገሩት ጥቅምት 25 ቀን 2018 ዓ.ም ምሽት 2 ሰዓት በትራንስፎርመሩ ላይ የደረሰው የእሳት አደጋ በጣቢያው ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር ተችሏል።

‎የጥገና ሥራው በራስ አቅም መከናወኑን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ይህም የጥገና ባለሙያዎች የልምድና የዕውቀት ሽግግር እንዲያገኙ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ገልፀዋል።

‎እንደ አቶ ደምስ ገለፃ በራስ አቅም የተከናወነው የጥገና ሥራ በስኬት መጠናቀቁ ህብረተሰቡን ለረጅም ጊዜ ከሚቆይ የኃይል መቋረጥ እንዲሁም ተቋሙን ከተጨማሪ ወጪ ታድጓል።

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top