የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል

የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል

ከጾታ ጥቃት ነፃ የሆነ ማህበረሰብ ለመገንባት ሁሉም የመፍትሔ አካል በመሆን የኃላፊነት ደርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ተገለፀ፡፡

ዓለም አቀፍ የፀረ ፆታ ጥቃት ቀን “ጥቃትን የማይታገስ ማህበረሰብ ለትውልድ ግንባታ” በሚል መሪ ቃል በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና መስሪያ ቤት ተከብሮ ውሏል።

በዓሉን አስመልክተው የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደተናገሩት ሴቶች ለሀገር ብልፅግና የሚያበረክቱትን የማይተካ ሚና ለማሳደግ ኋላ ቀር አመለካከቶችንና አስተሳሰቦችን በመቀየር የሴቶችን ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ ያስፈልጋል።

በተቋማችን ብሎም በሀገራችን  በሁሉም አካባቢዎች የሴቶችን ጥቃት የማይታገስ ማህበረስብ መፈጠር አለበት ያሉት ኃላፊው በሥራ ቦታዎች በሴቶችና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ለማስቆም ሁሉም አካል በጋራ ሊቆምና ሊሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

በተቋሙ የሴቶች እና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሌንሴ ኢደኤ እንደተናገሩት ከጾታ ጥቃት ነፃ የሆነ ማህበረሰብ ለመገንባት ሁሉም የመፍትሔ አካል በመሆን የድርሻውን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ በሥራና በሌሎች ቦታዎች በሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን ከመከላከል ጀምሮ የአመራርነትና ውሳኔ ሰጭነት ሚናቸውን በመደገፍ የተቋሙን ርዕይና ተልዕኮ ስኬት ላይ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ማገዝ ይገባል፡፡  

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና ህፃናት መብቶች ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰላማዊት ግርማይ በበኩላቸው በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚፈፀሙ ሥነ ልቦናዊ፣ ወሲባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና አካላዊ ጥቃቶችን ለመከላከል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ጾታዊ ጥቃትን ለመከላከል ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል የሥርዓተ ጾታ እኩልነትን የሚያረጋግጡ እና የኃይል ጥቃቶችን የወንጀል ድርጊት የሚያደርጉ የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ተግባራዊ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የሴቶችና የህፃናት መብቶች ከፍተኛ ባለሙያ ወ/ሮ ልደት ገ/ህይወት ሀገራችንን ከድህነት በማላቀቅ ከምትፈልገው ዕድገት ላይ እንድትደርስ እና ዜጎቿ የሚኮሩባት ሀገር እንድትሆን ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት በመከላከል ለሴቶች ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

በውይይቱ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ የተቋሙ ሠራተኞችም አካላዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ወሲባዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቃቶችን ለማስወገድ አስተማሪ የሆኑ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንደሚያስፈልጉ በመግለጽ ለተግባራዊነቱ የበኩላቸውን እንደሚያበረክቱ አረጋግጠዋል፡፡

ዓለም አቀፍ የፀረ ፆታ ጥቃት ቀን ዘንድሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ34ኛ ጊዜ፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ20ኛ ጊዜ እየተከበረ ይገኛል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top