ስርቆት የፈጸመው ግለሰብ በ10 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ

ስርቆት የፈጸመው ግለሰብ በ10 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት ተቀጣ

በጌዶ – ገፈርሳ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር ላይ ስርቆት የፈጸመ ግለሰብ በ10 ዓመት ከ6 ወር በሆነ ጽኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ አንድ ሪጅን አስታወቀ፡፡

በሪጅኑ የትራንስሚሽንና ኦፒጂ ደብሊው መስመር ጥገና ሥራ አስኪያጅ አቶ በፍቃዱ በቀለ እንዳስታወቁት የጌዶ -ገፈርሳ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የከፍተኛ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በተደጋጋሚ ሥርቆት ከሚፈጸምባቸው መስመሮች መካከል አንዱ ነው፡፡

መስከረም 11 ቀን 2018 ዓ.ም ሽብሩ ጉዲሳ የተባለው ግለሰብ ከተለያዩ የከፍተኛ ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ 35 ብረቶችን ፈቶ በጋሪ ጭኖ ሲሄድ በሸገር ከተማ አስተዳደር ገፈርሳ ጉጄ ክፍለ ከተማ በገፈርሳ ኤግዱ ወረዳ በህብረተሰቡ ጥቆማ በአካባቢው ሚሊሻዎች እጅ ከፍንጅ መያዙን ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

ጉዳዩን ሲከታተል የቆየው የሸገር ከተማ ከፍተኛ ፍርድ ቤትም ህዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት ግለሰቡን ከጥፋት ያርማል፤ ሌሎችንም ያስተምራል ያለውን የ10 ዓመት ከ6 ወር በሆነ ፅኑ እስራት እንዲቀጣ መወሰኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ  የኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች የአንድ ተቋም ብቻ ሳይሆኑ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀብት ናቸው ያሉት ሥራ አስኪያጁ ህብረተሰቡ በአካባቢው የሚገኙ መሰረተ ልማቶችን በኃላፊነት ስሜት ሊጠብቅ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

ማንኛውም ግለሰብ በኤሌክትሪክ መሰረተ ልማቶች ላይ ስርቆት የሚፈጽሙ ግለሰቦችን ሲመለከት በአካባቢው ለሚገኙ የጸጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠትና በማጋለጥ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡

ማስረጃዎችን በማሰባሰብ ጉዳዩ ውሳኔ እንዲያገኝ ክትትል ሲያደርጉ ለነበሩት ለገፈርሳ ጉጄ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ እና ለተቋሙ የህግ ክፍል የላቀ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top