የፕሮጀክቶችን አፈጻፃም ለማሻሻል እየተሠራ ነው

የፕሮጀክቶችን አፈጻፃም ለማሻሻል እየተሠራ ነው

ለኃይል መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች መዘግየት ምክንያት የሆኑ ውስጣዊ ችግሮችን በጥናት በመለየት የፕሮጀክት ትግበራን ለማሻሻል ከዴንማርክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በተመረጡ አራት ፕሮጀክቶች ላይ የዳሰሳ ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ፡፡

በዛሬው ዕለት በኮይሻ እና አይሻ 2 የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ የተካሄዱ ጥናቶች የመጀመሪያ ረቂቅ ሪፖርት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በተገኙበት ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፡፡

በተቋሙ የኮርፖሬት ፕላኒንግ ዘርፍ የዕቅድ ክትትልና ግምገማ ቢሮ ሥራ አስኪያጅ እና የጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ አቶ ቴዎድሮስ ዮሴፍ እንደተናገሩት ተቋሙ ከዴንማርክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ባለሙያዎች ጋር በመተባበር በአሰላ፣ በደቡባዊ ግሪድ ማስፋፊያ፣ በአይሻ 2 እና በኮይሻ የውሃ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ላይ የዳሰሳ ጥናት እያካሄደ ይገኛል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ የፕሮጀክቶቹን ባለቤት፣ ሥራ ተቋራጭን እና የአማካሪ ድርጅቶቹን የሥራ ኃላፊዎችን እና ሠራተኞች እንዲሁም የአካባቢውን ማህበረሰብና የመስተዳድር አካላት ባሳተፈ መልኩ መከናወኑን ገልፀዋል፡፡

ጥናቱ ተቋማዊ ዕውቀትና ትምህርት፣ የኮንትራት ሰነድ ዝግጅት፣ በፕሮጀክት ቢሮዎችና ሌሎች የሥራ ክፍሎች መካከል ስላለው ግንኙነትና የትብብር ሥራ፣ የኮርፖሬት ማህበራዊ ኃላፊነትን ከመወጣጥ አኳያ ፕሮጀክቶች ስላሉበት ደረጃ፣ ሥራ ተቋራጮችና አማካሪዎች ከሌሎች መንግስታዊ ተቋማት ጋር ስላላቸው ግንኙነት፣ የክትትልና ግምገማ ሥርዓት እንዲሁም የፕሮጀክት ትግበራ ዕቅድ በሚሉ ሰባት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

ከዚህ በፊት ከተከናወኑ ፕሮጀክቶች የተገኙ ዕውቀቶችን ለቀጣይ ግብዓት በሚሆን መልኩ አደራጅቶ ያለማስቀመጥ፣ የኮንትራት ሰነዶች ግልጽነት የጎደላቸው መሆናቸው፣ ግምገማዎች ከውስጣዊ ይልቅ ውጫዊ መሆናቸው፣ በፕሮጀክት ቢሮዎችና ሌሎች የሥራ ክፍሎች መካከል ያለው የትብብርና የግንኙነት ሥራ የተጠናከረ አለመሆን እንዲሁም ግልጽ የሆነ የማህበራዊ ኃላፊነት ማስተግበሪያ ዕቅድ ያለመኖር ክፍተቶች እንዳሉ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ የፕሮጀክቶቹን አፈፃፀም ለማሻሻል የሚያስችሉ አሰራሮችን ለመተግበር እንዲሁም የክትትልና ግምገማ ሥራዎች የሚከናወኑበትን አቅም ለማሳደግ እንደሚያግዝ በመጠቆም ውይይቱ ጥናቱ የደረሰበትን የመጀመሪያ ረቂቅ ሪፖርት ለሚመለከታቸው አካላት በማቅረብ ግብዓት ለመሰብሰብ ያለመ እንደሆነም አቶ ቴዎድሮስ አመላክተዋል፡፡

በደንማርክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ከፍተኛ አማካሪና የጥናቱ አባል የሆኑት ሚስተር ፒተር ሀዩለር በበኩላቸው በሀገራቸው ያሉ የኢነርጅ ተቋማት በፕሮጀክት ትግበራ ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችና የተገኙ ተሞክሮዎች በአግባቡ ተሰንደው የሚያዙበትና ሌሎች በቀላሉ የሚያገኙበት፣ የፕሮጀክት መረጃዎች ለበላይ አመራር ለውሳኔና ክትትል በሚመች መልኩ የሚቀርቡበት ሥርዓት መኖሩን እና ከፕሮጀክት ጽንሰ ሃሳብ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ያለውን ሂደት ለመምራት የሚያስችል “ስቴጅ ጌት” የሚባል ሞዴል ጥቅም ላይ እንደሚያውሉ አስረድተዋል፡፡

ተቋማቱ እየተገበሯቸው ያሉ ልምዶችን ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እያካፈሉ መሆኑን ገልፀው የፕሮጀክቶችን አፈፃጸም ለማሻሻል የተለያዩ ማመሳከሪያዎችንና ናሙናዎችን በማዘጋጀት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባም አስታውቀዋል፡፡

የፕሮጀክቶችን አፈፃጸም ለማሳደግ ቀድሞ ከተገነቡ ፕሮጀክቶች የተገኙ ተሞክሮዎችን በሌሎች ላይ ማስፋት እና የማህበረሰብ ተሳትፎና የማህበራዊ ኃላፊነት ሥራዎች ሊጠናከሩ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በኤጀንሲው አማካሪና የጥናቱ አባል የሆኑት ደረጄ ፈንቴ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ተቋሙ በቀጣይ የሚከናወኑ የፕሮጀክቶችን አፈጻጸም ለማሻሻል በጥናቱ የተገኙ ግኝቶችን በአግባቡ መተግበር እንደሚገባው የተናገሩት አማካሪዎቹ ለዚህም ድጋፎችን ከማድረግ ጀምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ከተቋሙ ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

በውይይቱ ላይ በመገኘት የማጠቃለያ ሃሳብና አቅጣጫ የሰጡት የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ እንደተናገሩት ተቋሙ ከፍተኛ በጀት በመመደብ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን እያከናወነ ቢሆንም በተያዘላቸው ጊዜና ወጪ በማጠናቀቅ በኩል ግን ክፍተቶች ይስተዋላሉ፡፡

የዳሰሳ ጥናቱ በቀጣይ የሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ውጤታማ እንዲሆኑ በግብዓትነት እንደሚያግዝ በመጠቆም ማንኛውም የፕሮጀክት አመራር ከዚህ በፊት የነበሩ ችግሮችን እየቀረፈ መሄድ፣ከፕሮጀክቶች የሚገኙ እውቀቶችን አደራጅቶ በመያዝ ለቀጣየይ የማስተላለፍ፣ የፕሮጀክት ሪፖርቶችን ወጥነት፣ ግልጽና ወቅታዊ በሆነ መልኩ ማዘጋጀት፣ የፕሮጀክት አጠቃላይ መረጃዎች ለውሳኔ አሰጣጥና ለክትትል በሚመች መልኩ የሚገኙበት አሰራርን መዘርጋት እና የክትትልና ግምገማ ስርዓቱን ማጠናከር እንደሚገባም አቅጣጫ ሰጥተዋል፡፡

በዳሰሳ ጥናቱ ወሰን ላይ በራስ ኃይል ከሚከናወኑ ፕሮጀክቶች ጭምር ማካተት እንደሚያስፈልግና በጥናቱ ግኝት ላይ ሌሎች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተጨማሪ ውይይቶችን በማድረግ በወቅቱ መተግበር እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል፡፡

በዕለቱም በጥናቱ ግኝት ላይ መሻሻል እና መካተት ይገባቸዋል የሚሉ አስተያየቶችና ጥያቄዎች ከተሳታፊዎች ቀርበው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top