ሪጅኑ የአሰራር ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ማድረጉን ገለፀ

ሪጅኑ የአሰራር ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያስችል መተግበሪያ ይፋ ማድረጉን ገለፀ

በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማዕከላዊ 1 ሪጅን የአሰራር ሥርዓቱን ለማዘመን የሚያስችል የኦፕሬሽን፣ ክትትል እና ጥገና የአሰራር ሥርዓት (Operation, Inspection, and Maintenance Management System) የተሰኘ የሞባይል እና የድረ-ገፅ መተግበሪያ በሥራ ላይ ማዋሉን አስታወቀ።

ሪጅኑ የማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና የማስተላለፊያ መስመሮችን የኦፕሬሽንና ጥገና ሥራዎች ለማሳለጥ በሚያግዘው መተግበሪያ ዙሪያ ለሠራተኞቹ ሥልጠና ሰጥቷል፡፡

በዚሁ ሥልጠና ወቅት የሪጅኑ ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ገዛኸኝ እንደገለፁት መተግበሪያው በኦፕሬሽን እና ጥገና ሥራዎች ላይ ቀልጣፋና በመረጃ ላይ የተመሰረተ የአሰራር ሥርዓት እንዲኖር በር የከፈተ ነው።

መተግበሪያው በሥራ ላይ ሲውል የኦፕሬሽን፣ ክትትል እና ጥገና የአሰራር ሥርዓቶች ከወረቀት ንክኪ ነፃ በማድረግ ለማዘመን፣ ጠንካራ የሀብት ቁጥጥር ሥርዓት ለመዘርጋት እና ወጪ ለመቀነስ እንዲሁም ሥራን ለማቀላጠፍ ሚናው የጎላ መሆኑን አመላክተዋል፡፡

በየዕለቱ በኃይል ማከፋፈያ ጣያዎች ውስጥ የሚመዘገቡ መረጃዎች ወጥነት የሌላቸው እንደነበሩ የገለፁት ዳይሬክተሩ የመተግበሪያው ወደ ሥራ መግባት ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚያግዝ ተናግረዋል፡፡

እንደ አቶ ደረጄ ገለፃ መተግበሪያው የሀብት አስተዳደር፣ የዕቅድ እና የሠራተኞች የብቃት ምዘና ሥርዓቶችን በውስጡ ያካተተ ነው፡፡

ዘመናዊ የአሰራር ሥርዓቱን በሁሉም ሪጅኖች ተግባራዊ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን የገለፁት አቶ ደረጄ በአሁኑ ወቅት የማዕከላዊ 2 እና 3 ሪጅኖችን በማሰልጠን የትግበራ ሙከራ መጀመሩን አብራርተዋል፡፡

መምሪያው የሪጅኑ ሠራተኞች ከመደበኛ ሥራዎቻቸው ባሻገር ያሏቸውን ተሰጥዖዎች በመጠቀም የሚያከናውኗቸውን የፈጠራ ውጤቶች ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑንም ነው ዳይሬክተሩ የገለፁት።

በሪጅኑ የቴክኒክ ባለሙያና የመተግበሪያው ፈጣሪዎች የሆኑት አቶ ደሳለኝ ተገኝ እና እያየሁ ደሴ እንደገለፁት የኦፕሬሽን፣ ክትትል እና ጥገና የአሰራር ሥርዓት መተግበሪያ የሪጅኖችን የመረጃ ልውውጥ ሥርዓት አንድ ደረጃ ከፍ የሚያደርግ ነው።

ተቋሙ የሚያስተዳድራቸው አብዛኞቹ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችና የማስተላለፊያ መስመሮች የተሟላ መረጃ የሌላቸው መሆኑ መተግበሪያውን ለማዘጋጀት እንዳነሳሳቸውም ነው የተናገሩት፡፡

መተግበሪያው በሙከራ ደረጃ ሥራ ላይ መዋል ከጀመረ ጊዜ አንስቶ የኦፕሬሽን እና ጥገና ሠራተኞች ትክክለኛና ወጥ የሆኑ መረጃዎችን በወቅቱ እየመዘገቡ በመሆኑ በሪጅኑ ኃይል ተቋርጦ የሚቆይበት ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱንም ነው ያስረዱት፡፡

የኦፕሬሽን፣ ክትትል እና ጥገና የአሰራር ሥርዓት (Operation, Inspection, and Maintenance Management System) የተሰኘው መተግበሪያ በሁሉም የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎች ውስጥ የሚገኙትን የትራንፎርመር ዓይነቶችና መጠናቸውን፣ የወጪና ገቢ መስመሮችን እና የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን ብዛት እንዲሁም መስመሮቹ ኃይል የሚያቀርቡባቸውን አካባቢዎች ጭምር ያካተተ ነው ብለዋል።

የማዕከላዊ 1 ሪጅን ከ 132 እስከ 400 ኪሎ ቮልት መጠን ያላቸው 21 የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያዎችን እና ከ1 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር በላይ ርዝመት ያላቸው የኃይል ማስተላለፊያ መስመሮችን በማስተዳደር ላይ ይገኛል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top