ተቋሙ የመሰረተ ልማት ስርቆትን በዘላቂነት ለመከላከል እየሰራ ነው

ተቋሙ የመሰረተ ልማት ስርቆትን በዘላቂነት ለመከላከል እየሰራ ነው

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በሚያስተዳድራቸው የኃይል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈፀሙ ስርቆቶችን ለመከላከል የተለያዩ አሰራሮችን በመዘርጋት እየሠራ እንደሆነ የተቋም ደህንነትና አስተዳደራዊ ጉዳዮች መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ከሊል ሽፋ እንዳስታወቁቱ በኃይል ማስተላለፊያ መስመር ተሸካሚ ምሰሶዎች ላይ የሚፈጸሙ የስርቆት ድርጊቶች ተቋሙን ለኪሳራ ከመዳረጋቸው ባሻገር ኃይል እንዲቋረጥ በማድረግ ህብረተሰቡን ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እያጋለጡት ይገኛሉ፡፡

በኃይል መሰረተ ልማት ላይ የሚደርስ ጉዳት በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትለውን አሉታዊ ተጽዕኖ በመገንዘብ ተቋሙ ደህንነቱን ለማረጋገጥ የሚያስችል የሥራ ክፍል ከማደራጀት ጀምሮ ስርቆት በስፋት በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች በህብረተሰቡና በሚሊሻ ማስጠበቅ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት በአምስት ሪጅኖች ውስጥ የሚገኙ 1 ሺህ 411 ምሰሶዎች በሰው ኃይል እየተጠበቁ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ከሊል አዲስ አበባ ዙሪያ ኮዬ ፈጨ፣ አዋሽ አርባ እና 7 ኪሎ፣ ሀዋሳና ሻሻመኔ ዙሪያ፣ ወላይታ ሶዶ እና ሳዉላ በሰው ኃይል ጥበቃ እየተደረገባቸው ካሉ አካባቢዎች መካከል እንደሆኑ አብራርተዋል፡፡

ይሁንና ማህበረሰቡ እንዲጠብቃቸው በተሰጡ ምሰሶዎች ላይ ስርቆት ቢፈፀምና የስርቆት ወንጀል ፈጻሚዎች የማይያዙ ከሆነ ቀበሌዎችና ወረዳዎቹ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱና ተጠያቂ እንደሚደረጉ ከስምምነት መደረሱን አስታውቀዋል፡፡

የታወር ክትትልና ቁጥጥር የሚያደርጉ የመከላከያ ሠራዊት የቀድሞ አባላት በመከላከያ ሚኒስቴር እና በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ስልጠና ተሰጥቷቸው በሪጅኖቹ መመደባቸውን አንስተዋል፡፡

እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ ስርቆትን በዘላቂነት ለማስቀረት እያንዳንዱ መስመር በሚያልፈበት አካባቢ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችንና የጸጥታ አካላትን በማወያየት ህብረተሰቡ ለመሰረተ ልማቱ በእኔነት ስሜት ጥበቃ እንዲያደርግ ታቅዶ እየተሰራ ነው፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top