ለቱሉ ካፒ የወርቅ ማውጫ ኩባንያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ በዕቅድ ተይዞ የነበረውን የጊምቢ- ቱሉ ካፒ ባለ 132 ኪሎ ቮልት የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና ማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀክት ግንባታን በይፋ ለመጀመር እየተሰራ መሆኑን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የትራንስሚሽን ቢዝነስ ገለፀ።
በዘርፉ የፕሮጀክት ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ አዛርያ ምናሴ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ከጊምቢ እስከ ቱሉ ካፒ የሚዘረጋ የ43 ኪሎ ሜትር የማስተላለፊያ መስመር፣ አንድ አዲስ የማከፋፈያ ጣቢያ ግንባታ እና በጊምቢ ነባር ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ የማስፋፊያ ሥራዎችን ያጠቃልላል፡፡
የፕሮጀክቱን የግንባታ፣ ዕቃ አቅርቦትና የማማከር ሥራዎች የቻይናው ሲኖ ሀይድሮ ኮርፖሬሽን እንዲያከናውን ስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢሆንም በጸጥታ ችግር ምክንያት ሥራ ተቋራጩ በወቅቱ ወደ ሥራ መግባት ባለመቻሉ ከኩባንያው ጋር የነበረው የግንባታና የማማከር ውል ተቋርጦ ለተቋሙ የኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ መሰጠቱን አስታውቀዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም የፕሮጀክቱን የግንባታ ሥራ በይፋ ለማስጀመር መስመሩ የሚያልፍበትን አካባቢ ከወሰን ማስከበር ነፃ ለማድረግ እና የማከፋፈያ ጣቢያው የሚገነባበት ቦታን ከወርቅ ማዕድን ማውጫ ኩባንያዉ ለመረከብ ከኩባንያውና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይቶች እየተካሄዱ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡
ሥራውን የሚያከናውነው የተቋሙ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት ቢሮ አዲስ ግንባታ የሚከናወንበት ቦታ እስከሚረከብ ድረስ በነባሩ የጊምቢ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ለወጪ መስመር የሚሆኑ የማስፋፊያ ሥራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ለፕሮጀክቱ የሚያስፈልጉ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዕቃዎች በአቅራቢው የሲኖ ሀይድሮ ኮርፖሬሽን በኩል አዲስ አበባ መድረሳቸውንም ጠቁመዋል፡፡
በኢንጅነሪንግና ኮንስትራክሽን ቢዝነስ የኮንስትራክሽን ማኔጅመንት 1 ፕሮጀከቶች ቢሮ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሀብታሙ ተሾመ በበኩላቸው የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራን የሳይት ርክክብ ከተካሄደበት ቀን ጀምሮ ባሉት 13 ወራት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ስምምነት ተደርሶ ከወዲሁ የተለያዩ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የፕሮጀክቱ የግንባታ ሥራ የሚከናወንበት ቦታ ርክክብ ባይፈጸምም ፕሮጀክቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ ከህዳር 10 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ሳይት በመግባት በጊምቢ ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ሥራዎች መጀመራቸውን አመልክተዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ዞን የሚገነባው የጊምቢ- ቱሉ ካፒ የኃይል ማስተላለፊያ መስመርና የማከፋፈያ ጣቢያ ፕሮጀከት ለቱሉ ካፒ የወርቅ ማዕድን ማውጫ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ ታስቦ የተቀረጸ ቢሆንም ከዚሁ ጎን ለጎን ለገንጅ ወረዳና አካባቢው ኃይል ለማቅረብ እና የብሔራዊ የግሪድ ሲስተሙን ለማጠናከር ያስችላል፡፡
💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”