በጣቢያው ሲከናወን የቆየው የአቅም ማሳደግ ሥራ ተጠናቀቀ

በጣቢያው ሲከናወን የቆየው የአቅም ማሳደግ ሥራ ተጠናቀቀ

በለገጣፎ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ላይ ሲከናወን የቆየው የአቅም ማሳደግ ሥራ መጠናቀቁን የማዕከላዊ 1 ሪጅን መምሪያ አስታወቀ፡፡

የመምሪያው ዳይሬክተር አቶ ደረጄ ገዛኸኝ እንዳስታወቁት የአቅም ማሳደግ ሥራው በጣቢያው አንድ ባለ 125 ሜጋ ቮልት አምፒር ተጨማሪ ትራንስፎርመር በመትከል የተከናወነ ነው፡፡

በዚህም የጣቢያውን ኃይል የመጫን አቅም ከ250 ሜጋ ቮልት አምፒር ወደ 375 ሜጋ ቮልት አምፒር ከፍ ማድረግ ተችሏል፡፡

የአቅም ማሳደግ ሥራው በዋናነት የለገጣፎ-ቱለፋ-ደብረብርሃን-ሸዋሮቢት ባለ 132 ኪሎ ቮልት የማስተላለፊያ መስመርን ኃይል የመሸከም አቅም ለማጠናከር መሆኑን ገልፀዋል።

ለለገጣፎ፣ ለምስራቅ አዲስ አበባ እና አካባቢዎች ተጨማሪ የኃይል ፍላጎት ጥያቄዎች ምላሽ ለመስጠት እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

የአቅም ማሳደግ ሥራው በሪጅኑ የጥገና ባለሙያዎች መከናወኑ ለዕውቀት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር በር የከፈተና ከ 20 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ማዳን ያስቻለ መሆኑንም ነው ያብራሩት፡፡

የለገጣፎ የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ታምራት ፎጊ እንደተናገሩት የጣቢያው የአቅም ማሳደግ ሥራ ከተለያዩ ማከፋፈያ ጣቢያዎች የመለዋወጫ ዕቃዎችን በማሰባሰብ የተከናወነ ነው።

ለሥራውም ከ7 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ ተደርጓል ብለዋል፡፡
 
ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኘው የለገጣፎ ባለ 230 ኪሎ ቮልት የኃይል ማከፋፈያ ጣቢያ  7 ባለ 230 ኪሎ ቮልት ገቢ መስመሮች እንዲሁም 2 ባለ 132፣ 15 ባለ 15 እና 5 ባለ 33 ኪሎ ቮልት ወጪ መስመሮች አሉት፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top