አመራሩ በመልካም ሥነ ምግባር በመታነጽ ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን መታገል አለበት

አመራሩ በመልካም ሥነ ምግባር በመታነጽ ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን መታገል አለበት

አመራሩ በመልካም ሥነ ምግባር በመታነጽ ሙስናን እና ብልሹ አሰራርን መታገል እንዳለበት በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ መምሪያ ገለፀ፡፡

መምሪያው ለተቋሙ መካከለኛ አመራሮች በሥነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ሕጎችና ጽንሰ ሀሳቦች ላይ ያተኮረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠና እየሰጠ ይገኛል፡፡

ሥልጠናውን በንግግር የከፈቱት የተቋሙ የዋና ሥራ አስፈፃሚ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሙላት ገዛኸኝ እንደተናገሩት የመካከለኛ አመራሩ ግልጽነትና ተጠያቂነትን በማስፈን ሙስናና ብልሹ አሰራርን በመታገል በኩል ከፍተኛ ሚና አለው፡፡

ተቋሙ የሚያከናውናቸውን ፕሮጀክቶችና የኦፕሬሽን ሥራዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመፈጸም መካከለኛ አመራሩ በጥሩ ሥነ-ምግባርና አሰራር የታነፀ ሆኖ መገኘት ይኖርበታል ብለዋል፡፡

ሥልጠናው ግልፅነትና ተጠያቂነት ያለበት የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ተቋማዊ የሪፎርም ሥራዎችን ለማሳካት የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

በተቋሙ የሥነ-ምግባርና ፀረ-ሙስና መከታተያ መምሪያ ዳይሬክተር አቶ ደረጀ አጥናፌ በበኩላቸው በበጀት ዓመቱ ከ3 ሺህ በላይ አመራሮችንና ሠራተኞችን በሙስና ምንነት፣ በፀረ-ሙስና ሕጎችና ጽንሰ ሀሳቦች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥልጠና ለመስጠት ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡

የመካከለኛ አመራሮች የሚያከናውኗቸውን ተግባሮች ሕግና መመሪያን የተከተሉ እንዲሆኑ በማድረግ ሙስናና ብልሹ አሰራርን አስቀድሞ በመከላከል ረገድ ያለባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ሥልጠናው በነገው ዕለትም የሚቀጥል ሲሆን በቀጣይ ለኃይል ማመንጫና ማከፋፈያ ጣቢያዎች የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች እንደሚሰጥ አብራርተዋል፡፡

💡 “ንፁህ ኢነርጂ ለተሻለ ህይወት!”

Scroll to Top